የጎንደር ቤተሰብ!

65

ባሕር ዳር:ጥር 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ቀድሞ ነገር “እንግዳ መጥቶብኝ ያውም የጎንደር ሰው፤ ያለጤፍ እንጀራ ያለ እርጎ ማይቀምሰው” እየተባለ ነበር የሚዘፈንለት፡፡ ጎንደሬ እንግዳ ሲኾን “ጎንደሬ ገደርዳሬ” ቢባልም እንግዳ ሲቀበል ግን “አፈር ስኾን” እያለ ነው፡፡ ይኽ የእንግዳ አክባሪነት ባሕል ከታሪክ የተሻገረ እውነት፤ ከልምድ የተዋደደ ማንነት እንደኾነ ማሳያ የዘንድሮው ጥምቀት አንዱ ኹነት ነበር፡፡

የተባረከ ሕዝብ ሀገሩን በመልካም ያስነሳል፤ ለልጆቹ በጎ ነገርን ያወርሳል። የታደለ ትውልድ ቀደምቶቹን ያስመሰግናል፤ ሀገረኛ ሥሪቱን ለቀሪው ዓለም በቀላሉ ያስተዋውቃል። የቀደመ ማንነቱን ያልረሳ ትውልድ የማያውቀው ኹሉ በስማ በለው ሊያየው ይመኛል፤ እግር የጣለው እንግዳ ኹሉ ያደንቀዋል። ምስጋና ለልጆቿ ይድረስና ጎንደር በዘንድሮው የጥምቀት በዓል እንዳትረሣ ኾና ተዋውቃለች።

እንግድነት በቀደምት ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ክቡር አደራ ነው። “ጥቁር እንግዳ” እየተባለም በልዩነት ይቀማጠላል። “ከፍትፍቱ ፊቱ” የሚል በሳል ብሂል ያላቸው ኢትዮጵያዊያን ለሀገሩ ባዕዳ፤ ለሰው እንግዳ የሆነን ኹሉ እንደ ብርሌ ተንከባክበው፤ እንደ ንጉስ አክብረው ቤተኛ ማድረግ ልዩ መገለጫቸው ነው። ፍቅራቸውን አሸክመው፤ ሥማቸውን አሳትመው መላክ መለያ ባሕሪያቸው ነው።

ማንም ቢጠየቅ ያለጥርጥር የሚመልሰው እና የሚያስታውሰው ከቀደምቷ ኢትዮጵያ ልዩ እና ነባር እሴቶች መካከል አንዱ እንግዳን ማክበር እና በፍቅር መቀበል ነው። ጥንት ኢትዮጵያዊያን እንግዶቻቸውን በጨዋ ደንብ ተቀብለው፤ በመልካም መስተንግዶ አቀማጥለው መሸኘትን ተክነውበታል። ለዚያም ይመስላል ኢትዮጵያን የረገጡ የባሕር ማዶ ሰዎች ኹሉ ልባቸውን ጥለው ትዝታቸውን አንጠልጥለው ለመመለስ የሚገደዱት።

ጎንደር ኢትዮጵያዊ ማንነቷን፤ አማራዊ ሥሪቷን ለቀሪው ዓለም ሁሉ በጥምቀት በዓል በድጋሚ አሣይታለች። ኢትዮጵያዊያን በጎንደር በጎ ሥራ ኮሩ፤ የኢትዮጵያ ወዳጆችም መልካም ነገርን ከአማራ ምድር ገበዩ።
የጎንደር ቤተሰብ የተሰኘው በጎ ተግባር ባለቤቱ የከተማዋ አውራ ተቋም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተሞክሮ ነው። ከኹሉም የሀገሪቱ ክፍል የተቀበላቸውን ተማሪዎች “የጎንደር ቤተሰብ” እያለ ሲያስተዋውቅ እና ሲያዛምድ ጥቂት ዓመታት ተቆጥረዋል።

ብልሕ ሕዝብ ከራሱ ይማራልና የጎንደር ከተማ ሕዝብ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ልቆ ተማረ። አልጋ ያጡ እና ዘግይተው የመጡ “ቤት ለእምቦሳ” ባይ የጥምቀት እንግዶቹን “እምቦሳ እሠሩ” እያለ ፊቱን አፍክቶ በሩን ከፍቶ በደስታ ተቀበላቸው። እልፍኝ ከአዳራሽ ለእንግዶች ክብር ተለቀቀ። እንግዳ በታላላቅ ግቢዎች በተተከሉ ድንኳኖች ተጥለቀለቀ። ጎንደር በጥምቀት አብዝታ ተባረከች።

አሚኮ ካነጋገራቸው የጎንደር እንግዳ ተቀባዮች መካከል የጨዋ ሠፈሯ ወይዘሮ ውባለም ብርሃኑ “ቤት የእግዚዓብሔር ነው፤ እንግዳም በረከት ነው” ይላሉ፡፡ በዚህ የኑሮ ውድነት ዘመን አንድ ቤተሰብ ስድስት እንግዶችን ተቀብሎ ማስተናገድ ከባድ ቢመስልም እንግዳን መቀበል ባሕላቸው ያደረጉት ጎንደሮች ችለውበታል፡፡ “እግር ጥሏችሁ ወደ እኛ ቤት ጎራ አላችኹ እንጂ ኹሉም የጎንደር ሰው እንግዶችን ተቀብሎ እያስተናገደ ነው የሚሉት ወይዘሮ ውባለም ሊጠይቁን መጥተው ለምን ተንገላትተው ይመለሣሉ ይላሉ፡፡

“ኢትዮጵያዊ በመሆኔ በእውነት ኮርቻለሁ” ያሉን ደግሞ ከአዳማ የመጡት የጎንደር እንግዳ አቶ ምትኩ ተሰማ ናቸው፡፡ የአማራ ምድርን ሲረግጡ እና ጎንደር ሲመጡ የመጀመሪያቸው እንደሆነ የነገሩን አቶ ምትኩ የገረመኝ ነገር ቢኖር ከልጅ እስከ አዋቂ እንግዳ ተቀባይነታቸው ፍጹም ትሕትና የተሞላበት መሆኑ ነው ይሉናል፡፡ እኔ ጉራጌ ነኝ የሚሉት የጎንደር ቤተሰብ ፤ ቦረና ብትሄዱ ይህንን እንግዳ ተቀባይነት ታያላችሁ፤ በበዓል ወደ ጉራጌ ብታቀኑ ይህንን መቀበል ታገኛላችሁ እናም ኢትዮጵያ የተለየች ምድር እንደኾነች የገባኝ አኹን ነው ይላሉ፡፡

“ከዚህ በኋላ ጎንደርን መርሳት እንዴት ይቻላል” የሚሉት የጥምቀት እንግዳ እና የጎንደር ቤተሰቡ አቶ ምትኩ ያላዩት ሊያዩት የሚገባ፤ ላልሰሙት ልንናገረው የምንገደድ እውነት ቢኖር ጥምቀትን በጎንደር መታደም ነው ብለዋል፡፡

ጎንደር ቀደምትነቷን አስመሰከረች፤ ማንነቷን በተግባር ተናገረች፡፡ የጎንደር ቤተሰብ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተጀምሮ በጥምቀት ደምቆ ታየ፡፡ የጎንደር ቤተሰብ የጎንደር ምስክር፤ የአማራ ሕዝብ ክብር ነው፡፡ ጎንደርን ገና ከዚህ በላይ ኢትዮጵያዊነትን ስትገምድ እና ስታስተሳስር እናያለን፡፡ የዚያው ሰው ይበለን!

ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!