የግጭት ነጋዴዎች

118
ነጭመደበኛ
ነጭመደበኛ

ባሕር ዳር : ሚያዝያ 04/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ከሰባት ዓመታት በላይ በዘለቀው የየመናዊያን ምስቅልቅል ያተረፉ ቢኖሩ በአካባቢው የሚያንዣብቡት የአንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት የፖለቲካ ቁማርተኞች ብቻ ነበሩ፡፡ በየመን ግጭት ከአርብቶ አደር እስከ ሚኒስትር የችግሩ ዳፋ ያልጠበሰው እና ያላወየበው የመናዊ ግን ፈጽሞ አይገኝም፡፡
ከሊቢያ እስከ ሶሪያ፣ ከሩዋንዳ እስከ ዩጋንዳ መሰል የእርስ በርስ ግጭቶች ተፈጥረው ከተሞቻቸውን ዶግ አመድ፤ ዜጎቻቸውን ለስደት እና ሞት ዳርገው አልፈዋል፡፡ በርካታ የዓለም ሀገራት ካስተናገዱት የግጭት ፈተናዎች መካከል ሕዝባዊ አሰላለፍ እና ጎራ ያላቸው የሚመስሉ የእርስ በርስ ግጭቶች ቀዳሚውን ቦታ ይይዛሉ፡፡
በተደጋጋሚ እንደታየው በየሀገራቱ የተፈጠሩ ግጭቶች የውስጥ እና የእርስ በርስ ሽኩቻ መልክ ቢኖራቸውም የውጭ ግጭት ጠማቂ ባለሟሎች ረጃጅም እጆች እንዳልተለዩት ግን ይነገራል፡፡ “ለአንዱ ስንዴ ለሌላኛው ጎራዴ” የሚያስታጥቁትን የውጭ ኀይሎች ውስብስብ ሴራ የተቋቋሙ ሀገራት ተሞክሮ የሚያሳየው ደግሞ በፈተና የማይታጠፍ እና ለውጭ ኀይሎች ተጋላጭነት የማይመች ውስጣዊ አንድነት መኖሩን ነው፡፡
እምብዛም ጦርነት ተለይቷት የማታውቀው ኢትዮጵያ ሕዝብን መሰረት ያደረገ ግጭት ከትናንት እስከ ዛሬ ገጥሟት አያውቅም የሚሉት ብዙ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ከሚያለያያቸው የልዩነት ሰበዝ ይልቅ የሚያስተሳስራቸው የአርቦን ገመድ በእጅጉ ይበረታል፡፡ ጋብቻ እና ሃይማኖት፣ ባሕል እና ምጣኔ ሃብት፣ ታሪክ እና መልከዓ ምድር የኢትዮጵያዊያንን አብሮነት በጽኑ መሰረት ላይ ገምደውታል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ከልዩነት ይልቅ አብሮነት አማራጭ አልባ ተፈጥሯዊ ምርጫቸው ኾኖ ተሠርቷል፡፡
ከ1960ዎቹ መባቻ ጀምሮ የግጭት ነጋዴዎች የፖለቲካ ቅራኔን የፈጠሩ አዳዲስ የሀገረ መንግሥት አማራጮችን እና የፖለቲካ እሳቤዎችን ይዘው ብቅ አሉ የሚሉን በፖለቲካ ሳይንስ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪው ጋሻው አይፈራም ናቸው፡፡ እነዚህ የፖለቲካ ልሂቃን በጊዜ ሂደት ከግል ጥቅም መሻቶቻቸው ተነስተው የቡድን ፍላጎት ማዳበርን ቀስ በቀስ እንዳላመዱ አቶ ጋሻው አብራርተዋል፡፡ ይኽ ልምምድም ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ገደማ በሀገሪቱ ኹሉም አቅጣጫ ተበድያለኹ ብሎ የሚያስብ እና ቅራኔ ያደረበት የፖለቲካ አሰላለፍን ፈጥሯል ይላሉ፡፡
የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ በጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት ወጋግራ የቆመው ሕገ መንግሥት እና በልዩነት ላይ የተመሰረተው ብሔር ተኮር ፌዴራሊዝም ለሀገረ መንግሥት ቅራኔው መዋቅራዊ አደረጃጀት ሆነው አገልግለዋልም ይላሉ፡፡ ልዩነትን በንግግር እና በውይይት መፍታት ያልለመደው የሀገሪቱ የፖለቲካ ርእዮተ ዓለማዊ ባሕልም ለተደጋጋሚ ግጭት ሲዳርግ ተስተውሏል፡፡
የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት ግጭትን እንደ አማራጭ የወሰዱት የፖለቲካ ልሂቃን ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ እንደመጣ አቶ ጋሻው ተናግረዋል፡፡ ሀገሪቱም በርካታ ያልተሳኩ እና የተጠለፉ አብዮቶችን አስተናግዳለች ብለው ያስባሉ፡፡ በርካታ ወጣቶች የሕይወት መስዋዕትነት የከፈሉባቸው እና ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እስከ ዘመነ ሽብርተኛው ትህነግ የተደረጉት የተጠለፉ አብዮቶች በሀገሪቱ አሳታፊ እና የሰከነ የፖለቲካ ምህዳር መፍጠር ተስኗቸው ቆይተዋል ባይ ናቸው፡፡
ልዩነትን በንግግር እና በውይይት የመፍታት ባሕልን ያላዳበረው የሀገሪቱ ፖለቲካ እና ፖለቲከኞች አማራጭ ብለው የሚወስዱት መፍትሄ መታጠቅን ነው ብለዋል ምሁሩ፡፡ ይኽም በሀገሪቱ አሳታፊ የፖለቲካ ምህዳር እንዳይኖር አድርጎታል ነው ያሉት፡፡ የፖለቲካ ልሂቃኑ የጥቅም ግጭት እና ሽኩቻም የቡድን እና የሕዝብ ተደርጎ ሲወሰድ እንደተስተዋለ ጠቅሰዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ከሁሉም አቅጣጫ ያሉት የግጭት ነጋዴዎች በተደጋጋሚ የሚያስተባብሩትን ግጭት ሕዝባዊ መልክ ለማስያዝ ሲሞክሩ እንደሚታዩ ይናገራሉ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገሪቱ እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት በሂደት አካታች የፖለቲካ ምህዳር መፍጠር እንደሚያስፈልግ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ጠቁመዋል፡፡ ሌሎች ቢሆኖችንም ያስቀምጣሉ፡፡ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ማጠናከር፣ የመሰረተ ልማት ትስስርን ማስፋት፣ ዘላቂ ጥቅምን ማረጋገጥ እና የሰከነ የፖለቲካ ከባቢን መፍጠር ተገቢ እንደኾነ አመላክተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው