የግዮን በዓልን ለማክበር በርካታ እንግዶች ወደ ግሺ ዓባይ ከተማ እየገቡ ነው፡፡

0
133

ባሕር ዳር:ጥር 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የግሺ ዓባይ ከተማ 5ኛውን ዙር የግዮን በዓል ለማክበር ዝግጅቷን አጠናቃለች፡፡ የታላቁን ጻድቅ የአቡነ ዘርዓ ብሩክ ዓመታዊ በዓል እና የግዮንን በዓል ለማክበር ዝግጅቱ መጠናቀቁን የሰከላ ወረዳ አስታውቋል፡፡

የሰከላ ወረዳ አሥተዳዳሪ በላይነህ አድማሱ፤ የግሺ ዓባይ ከተማ የታላቁ የግዮን ወንዝ መነሻ፣ የታሪክ ማኅደር፣ የበርካታ ቅርሶች መገኛ እና የፈውስ ምድር ናት ብለዋል፡፡

ቦታውን ለማልማት እና የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ከታላቁ ጻድቅ ከአቡነ ዘርዓብሩክ ዓመታዊ በዓል ጋር ተያይዞ የግዮን በዓል ይከበራል ነው ያሉት፡፡

በበዓሉ ላይ ግዮንን ከምንጩ ለማልማት እና የግዮን ወንዝ መነሻ የኾነችውን የግሺ ዓባይ ከተማን ለመላው ዓለም ለማስተዋወቅ ያለመ ውይይትም ይካሄዳል ብለዋል፡፡ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት “ዓባይን ከምንጩ እንዴት እናልማው” በሚል ርዕሰ ጉዳይ የሚካሄደው የፓናል ውይይት እንዲኹም የአቡነ ዘረዓብሩክ ቤተክርስቲያን የቅኔ ምሽት የበዓሉ የዋዜማ ድምቀቶች እንደሚኾኑ አስረድተዋል፡፡

በሠከላ ወረዳ አትሌቶች “ስለ ዓባይ እሮጣለሁ” የሩጫ ውድድር፣ የአትሌቲክስ መንደር ጉብኝት፣ የታላቁ ጻድቅ የአቡነ ዘርዓብሩክ የንግሥ በዓል እና ፈረስ ግልቢያ በዕለቱ የሚከናወኑ ተግባራት መኾናቸውን አቶ በላይነህ ተናግረዋል፡፡

አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እየተሠራ ነው ያሉት አስተዳዳሪው የግዮን ወንዝ መነሻ፣ ጅምር የፋሲል ግንብ፣ የጉደራ ሐይቅ፣ የዓልዓዛር ዋሻ፣ ትክል ድንጋይ፣ የጅበላ ዋሻ እና “ድንጋይ ቀዳዳ” በወረዳው ከሚጎበኙ የቱሪዝም ቦታዎች ጥቂቶቹ እንደኾኑ አስረድተዋል፡፡

ጎብኝዎች የታላቁ የግዮን ወንዝ መነሻ፣ በተፈጥሮ እና ሠው ሠራሽ ቅርሶች በታደለው፤ መሬቱ የዘሩትን በሚያበቅለው፣ ሕዝቡ እንግዳ ተቀባይ በኾነው በግሺ ዓባይ ከተማ ተገኝተው አይረሴ ጊዜን እንዲያሳልፉ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

በዓሉን ለማክበር በርካታ እንግዶች ወደ ከተማዋ ገብተዋል ያሉት አስተዳዳሪው ዘግይተው የተነሱ እንግዶችንም ለመቀበል ዝግጅታችን ተጠናቋል ነው ያሉት፡፡

የከተራ እና የጥምቀት በዓል በሰላም ተጠናቅቋል ያሉት አስተዳዳሪው የአቡነ ዘርዓብሩክ ዓመታዊ እና የግዮን ዓመታዊ በዓል በሰላም ለማክበርም ዝግጅቱ መጠናቀቁን ነው ያስገነዘቡት፡፡

በትራንስፖርት በኩል የሚገጥመውን ችግር ለመቅረፍ ወረዳው ከምዕራብ ጎጃም ዞን እና ከአዊ ብሔረሰብ አስተዳዳር መንገድ እና ትራንስፖርት ጋር በቅንጅት እየሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡

ባለሃብቶች በኢንቨስትመንቱ እንዲሳተፉ እና መንግሥት የጀመረውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲደግፉ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን አስተዳዳሪው ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!