‹‹የጌታቸው ልጅ የመኳንንቱ ፣ የሙሉነሽ ልጅ የወይዘሮይቱ ፣ ክላሽ ማራኪ ከነ ጥይቱ››

0
588
‹‹የጌታቸው ልጅ የመኳንንቱ
የሙሉነሽ ልጅ የወይዘሮይቱ
ክላሽ ማራኪ ከነ ጥይቱ››
ባሕር ዳር፡ የካቲት 16/2013 ዓ.ም (አብመድ) መተረጌስ ሲያጎራ፣ ጥይት እንደ በረዶ ሲዘራ፣ ጦርነቱ ሲግል፣ በለው፣ ውጋው ፣ ጣለው ሲባባል ልብ ይፈተናል፡፡ በዚያ ፈታኝ ጊዜ ወደ ጦር ሜዳ መገስገስ፣ አልሞ መተኮስ ፣ ምሽግ ተራምዶ ማፈራረስ ጀግንነትን ይጠይቃል፡፡ ሀገር ሰላም ያሉት የከተማዋ ነዋሪዎች ሌሊቱ በሰላም ይነጋ ዘንድ ፈጣሪያቸውን ለምነው ተኝተዋል፡፡ ያቺ ሌሊት ከሁልጊዜዬው የተለዬች ነበረች፡፡ ጭር ባለው ሌሊት ገዳይ ጥይቶች ተሰሙ፡፡ በከተማዋ አናት ላይ የቡድን እና የግል መሳሪያዎች አጓሩ፡፡
May be an image of nature and skyበሰላም ተኝቶ በሰላም ማንጋት እንጂ በሌሊት ጦርነት ይሆናል ብሎ የገመተ አልነበረም፡፡ ለዓመታት የተደገሰው ድግስ በሌሊት ተቀዳ፡፡ የተኩስ ናዳ በዚያች ከተማ ፈነዳ፡፡ የተኩሱን ምክንያት ማወቅ፣ ጠላትን መመከትና ጎረሮ ለጎረሮ መተናነቅ ቀላል አልነበረም፡፡ ሳይታሰብ ለዚያውም በሌሊት ጦርነት ፈታኝ ነበር፡፡ ዳሩ መሸሽ የማያውቀው የጠገዴ ሰው የመጠውን ሊቀበል ነፍጡን እያወጣ ተኩሱ ወደ ተሰማበት በኩል አመራ፡፡
በዚያ ሌሊት ውጎያ የተከፈተባቸው የአማራ ልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላት በጉድባቸው ገብተው የመጠውን ወጀብ ይጋርዱ ጀምረዋል፡፡ ሀገር ማጥለቅለቅ ያሰበው ወጀብ እንዳሻው የሚራመድ፣ እንዳሻው የሚማርክና የሚያንበረክክ መስሎት ነበር፡፡ ሳያስብ የተመጣበት የጀግና ስብስብ አስቦ የመጣውን ጦረኛ አላሳልፍህ አለው፡፡ የመጀመሪያው ወጄብ ምሽግ ሊሰብር ተጋፋ፣ ጀግኖቹ አልቀመስ አሉ፡፡ ወደኋላ ተመልሶ ሌላ ኃይል አጠናክሮ ተመለሰ፤ አሁንም የሚቀመሱ አልነበሩም፡፡
ዘጠኝ ጊዜ የተለያዬ ማጥቃት አድርገውብናል ይላሉ የመጀመሪያው ገፈት ቀማሾች፤ ዘጠኙም አልተሳካም፡፡ ሳንጃ ቁርሱን ሊበላ የነበረው የትህነግ ቡድን ቅራቅርን መርገጥ ተሳነው፡፡ ምን ያ ብቻ አስቀድሞ ይኖርባት ከነበረችው ማክሰኞ ገበያ ከተማም መቆዬት ተሳነው፡፡ ማዕበሉ ፊቱን አዙሯልና አጥቂው ተጠቃ፣ በዚያ ሌሊት የተደረገው ጀብዱ ይደንቅ ነበር ይላሉ፤ ቅራቅር በዋዛ ተይዛ ቢሆን ኖሮ አካሄዱ ሊቀየር እንደሚችልም የሚናገሩ አሉ፡፡ ታዲያ ስፍራው ጀግኖች የኖሩበት፣ ጀግኖች የሚፈጠሩበት፣ አይበገሬዎች የሚፈልቁበት ነበርና፡፡
‹‹በሸሪፎ ጥይት ግንባሩን ካላሉት
አይመለስ ጠላት በሕግ አምላክ ቢሉት›› እያለ በውድቅት ሌሊት ይዋደቅ ጀመር፡፡ በሕግ አምላክ የተባሉበት ዘመን አልፏል፣ የሽምግልናው ዘር ፍሬ ሳያፈራ ቀርቷል፡፡ ቀደም ሲል ትህነግ ተኩስ በከፈተበት ሥፍራ የአማራና የትግራይ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የሕዝቦች ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ለውይይት ተቀምጠው ነበር፤ ትህነግ ግን የሽምግልናውን ውሳኔ አልተቀበለውም ነበር፡፡ በዚያ ለሳለም በተቀመጡበት ስፍራ ትህነግ ውጊያ ከፈተች፡፡
ትህነግ በቅራቅር ተኩስ ሲከፍት አያሌ ጀብዱዎች ተሰርተዋል፡፡ በዚያ ሌሊት ልጆቿን በቤት ዘግታ በእጇ መሳሪያ ሳይኖራት ወኔ ብቻ ታጥቃ የገባች አንዲት ጀግና አለች፡፡ የጀግንነቷ ልክ ምን ይደንቅ፣ የውሳኔዋ ነገር ምን ይረቅ፡፡
አበሩ ጌታቸው ትባላለች፡፡ የተወለደችው ጠገዴ ማክሰኞ ገበያ ነው፡፡ አስተማሪ ናት፡፡ ነዋሪነቷ በቅራቅር ከተማ ነው፡፡ የትህነግ የግፍ አገዛዝ ቤተሰቦቿን እና እርሷን አስመርሯል፡፡ የከፋው ዘመን አልፎ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ነጻ የሚወጣበት ጊዜ ይናፍቃት ነበር፡፡ ደግሞም አንድ ቀን ያ ነገር እንደሚፈጠር ተስፋዋ ከፍ ያለ ነበር፡፡ ያለችው አልቀረም የተስፋ ዘመን ራሱ ገፍቶ መጣ፡፡ ጨለማውን ገፍቶ ብርሃን ለማዬት ዋጋ መክፍል ቢያስፈልግም የነጻነት ጊዜ ቀረበ፡፡
ትህነግ በቅራቅር ተኩስ ሲከፍት አበሩ ምን አደረገች- ‹‹ የጦርነቱን ድምፅ የሰማሁት ከቤቴ ሆኜ ነው፡፡ ከእንቅልፌ ስነቃ ጥይት ይተኮሳል፣ ለማውቃቸው ፖሊሶችና ሚሊሻዎች ስልክ ደወልኩ፣ አይመልሱም፣ ከዚያ ከቤት ወጣሁ፣ ተከራዮች ተይ እትዬ ተረጋጊ እያሉኝ እንደዚህ እየተተኮሰ መቀመጥ አልችልም ብዬ ወጣሁ፤ ከዋና አስተዳደሪው ቤት ሄድኩኝ፣ ባለቤቱን ስጠይቃት ትህነግ በራሱ ጊዜ ጦርነት መክፈቱን፣ በየአካባቢው ያሉ መከላከያዎች እንደተመቱ ነገረችኝ›› አስቀድሞም መገፋት ያስመረራት ስሜቷን ተፈታተነው፤ ወኔዋን ቀሰቀሰው፣ መደፈር አመማት፣ መነካት አሻፈረኝ አሰኛት፡፡
የትህግ ታጣቂዎች ቅራቅርን ለመቆጣጠር መፋለም ላይ ናቸው፡፡ የአማራ ልዩ ኃይሎችና የጠገዴ ሚሊሻዎች የጥይት በረዶ እየዘነበባቸው የሚያነቃንቃቸው ጠፋ፡፡ ሌሊቱ እየነጋ ሄደ፣ የአርማጭሆ ሚሊሻና የአማራ ልዩ ኃይል ወደ ሥፍራው ገባ፡፡ ጦርነቱ ደመቀ፡፡ ኃይል ሚዛኗን ደፋች፣ የተገፋው ጦር እያሸነፈ ሄደ፡፡ ከጉድብ ጉድብ እያስነቀለ፣ እግር ከእግር እየተከተለ፣ መሳሪያውን እያስጣለ ያባርረው ጀመር፡፡ አበሩ ከሠራዊቱ ጋር ተቀላቀለች፡፡
‹‹እኔ እዘገዋለሁ ቤቴን እንደ አመሉ
ወዴት ሄደ ሲሉ ከፍቶት ሄደ በሉ›› እንዳለ አርበኛው ወዴት ሄደች ለሚለው ከፍቷት ሄዳለች ነበር መልሷ፡፡ በተከፋው ልቧ ወኔ ጨምራበት ያለ ምንም ፍረሃት ወደ ውጊያ ገባች፡፡ ‹‹ሶስት ልጆች አሉኝ፣ ልጆችሽን ትተሸ ተይ አትሂጂ አሉኝ፣ እኔ ግን አልተቀበልኳቸውም፣ ያን ቀን እናፍቀው ነበር፣ ለመመለስ ዓላማም ዕቅድም አልነበረኝም፣ የጦር መሳሪያ እጄ ላይ አልነበረም፣ ቢያንስ አንድ ኃይል ቢመታ አንስቼ እታገላለሁ ብዬ ነው የገባሁ›› አበሩ ቆረጠች፣ ልቧ ሸፈተ፡፡
ሠራዊቱ ያበረታታት ጀመር፡፡ መስዋእት እሆናለሁ እንጂ አልመለሰም አለች፡፡ በበረሃ በእግሯ ትጓዝ ጀመር፡፡ በዚያ ላይ ውጊያ አለ፡፡ ‹‹ተከዜን መርገጥ አለብኝ ብዬ ተጓዝኩ፣ ልጆቼን የማስታውሰው ከውጊያ ስናርፍ ነው፡፡ በተኩስና በጉዞ ሰዓት አላስታውሳቸውም፡፡ ለእኔ ጥሩ አጋጣሚ ነበር፡፡ ልጆቼ ወደ ጦር ሜዳ መሄዴን አያውቁም፣ የመጀመሪያው ልጄ የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ነው›› ነው ያለችው፡፡ ውጊያው ቀጠለ አበሩም ወደፊት ገሰገሰች፡፡ ወኔዋ የበለጠ እየጋለ ሄደ፡፡
‹‹ የጌታቸው ልጅ የመኳንንቱ
የሙሉነሽ ልጅ የወይዘሮይቱ
ክላሽ ማራኪ ከነ ጥይቱ›› ይህች ጀግና ዘምታ አሸንፋለች፣ ተኩሳ ጥላለች፣ ክላሽ እስከነ ጥይቱ ማርካለች፡፡ ‹‹ደጀና ላይ ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ ነበር፡፡ 11 ሰዓት አካባቢ እኛ ድል አድርገን ቦታውን ተቆጣጠርነው፡፡ ጦርነቱ አልቆ የእነርሱን ካምፕ ስንቆጣጠረው የመከላከያ ሠራዊት አባላትና የልዩ ኃይሉ የጦር መሪዎች ክላሽ ከእነ ሙሉ ትጥቁ ሸለሙኝ፡፡ ወልቃይት ላይ የትህነግ ታጣቂዎች በመኪና ሆነው ወደ ከተማ ሲገቡና ውጊያ ሲጀምሩ እኔም የውጊያው ተካፋይ ሆንኩ፡፡ በተሸለምኩት ክላሽ መታሁት፡፡ የያዘውን አርባ ጎራሽ ክላሽም ማረኩት›› ነበር ያለችን፡፡
ጊዜው አለፈ ፤ አበሩ ድል አየች፣ የተመኘችው ደረሰ፡፡ ከድል በኋላ የማኅበረሰቡ አቀባበል መልካም እንደነበርም ነግራናለች፡፡ ‹‹አሁን ደስተኛ ነኝ፣ ትህነግ ጠፍቶ ማኅበረሰቡ እንደፈለገ ሆኗል፣ ሴቶች ሳይሸማቀቁ የጎንደርኛ ቀሚስ እየለበሱ፣ ሳይሳቀቁ በአማርኛ እየተናገሩ ነው፡፡ እንደፈለጉ፣ እንደፈለግን የምንቀሳቀስበት እድል ተፈጥሯል፤ ይሄ ትልቅ ድል ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም ያልጠራ ነገር ስላለ ትግሉ ገና ነው›› ብላለች አበሩ፡፡
በወልቃይት ጠገዴ የልማት ሥራዎች መጠናከር አለባቸውም ነው ያለችው፡፡ የእርስ በእርስ ግንኙነትም መጠናከር አለበት ብላለች፡፡ ሴቶች ከወንዶች እኩል ከላበለዚያም በላይ ናቸውም ብላለች፡፡ አሁን ያ ጊዜ አልፏል፡፡ አበሩም ወደ ቀደመ ሥራዋ ተመልሳለች፡፡
በዚያ ሥፍራ አዲስ ነገር መጥቷል፤ ነጻነት አሸንፏል፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ