የገለጉ ከተማ ነዋሪዎች የንጹህ መጠጥ ውኃ ችግራቸው እንዲፈታ ጠየቁ።

20
ገንዳ ውኃ :መጋቢት 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከገለጉ ከተማ ውኃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው በገጠራማው የሀገሪቱ ክፍል አንድ ሰው በቀን 40 ሊትር ውኃ ማግኘት እንዳለበት በስታንዳርዱ ተቀምጧል። እስከ 25 ሺህ የሚጠጉ የቋራ ወረዳ ገለጉ ከተማ ነዋሪዎች ግን 10 ሊትር ውኃ እንኳ በቀን ማግኘት አልቻሉም።
በገለጉ ከተማ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች በከተማዋ ባጋጠመው የውኃ ችግር የወንዝና የጉድጓድ ውኃ ለመጠቀም መገደዳቸውን ነግረውናል።
ካነጋገርናቸው የከተማ ነዋሪዎች ውስጥ ሸዋየ መብራት እንደገለጹልን የንጹህ መጠጥ ውኃ ማግኘት ካቆሙ ከአራት ወር በላይ ኾኗቸዋል። በዚህ ምክንያት የአካባቢውን ሙቀት ለመቋቋም የወንዝና የጉድጓድ ውኃ ለመጠጥና ለንጽህና መጠበቂያነት ለመጠቀም ተገደዋል። ይህንን ለማግኘት ደግሞ በሌሊት ተጉዞ ከሦስት ሰዓት በላይ መጠበቅ ግድ ይላል ብለዋል። አንዳንዴም ውኃ ሳያገኙ የሚመለሱበት ጊዜ መኖሩን ነው የገለጹልን። ይህም ተማሪ ልጆቻቸውን መግበው ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ ፈትኗቸዋል።
የውኃ ችግሩ በግለሰቦች ብቻ ሳይኾን በመንግሥት ተቋማት ላይም ተጽዕኖ አሳድሯል። በችግሩ ሰለባ ከኾኑት ተቋማት መካከል ደግሞ የገለጉ ጤና ጣቢያ ይገኝበታል። የጤና ጣቢያው ተወካይ ኀላፊ አታላይ ነጋ እንዳሉት ባጋጠመው የውኃ ችግር ጤና ጣቢያው የተሟላ አገልግሎት እንዳይሰጥ አድርጎታል። በተለይም ደግሞ በእናቶች እና ሕጻናት ጤና ላይ፣ በላብራቶሪና ድንገተኛ ምርመራ ሥራቸው ላይ ችግሩ የጎላ መኾኑን ነው ያነሱት። ችግሩንም ለመቅረፍ ለበርሜል ከ100 ብር በላይ ወጭ በማውጣት በየቀኑ እስከ አራት በርሜል ውኃ ከወንዝ በማስመጣት እንደሚጠቀሙ አንስተዋል።
የቋራ ወረዳ ገለጉ ከተማ ውኃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ምላሹ አሰፋ አካባቢው የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር ውኃ አቅም ቢኖረውም ውኃ ለመግፋት በሚያገለግለው ጀኔሬተር ብልሽት፣ በነዳጅ ዋጋ መናር ችግር እና ለከተማው ነዋሪ የሚያሰራጨው የውኃ ታንከር የተቀመጠበት ቦታ ዝቅተኛ መኾን ምክንያቶች ለነዋሪው ውኃ ተደራሽ ለማድረግ አልተቻለም።
ችግሩን ለመፍታት በጀነሬተር የሚገፋውን ውኃ በኤሌክትሪክ ለመግፋት የማስፋፊያ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። በአንድ ሳምንት ውስጥም ችግሩ እንደሚፈታ አንስተዋል።የውኃ ማጠራቀሚያ ታንከሩን ችግር ለመፍታት ግን ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!