‘‘የድንች ምርት እስከ 60 ኩንታል በሄክታር ቀንሷል፡፡’’ ያነጋገርናቸው የደቡብ ጎንደር ዞን አርሶ አደሮች፡፡

0
151

‘‘ከበሽታ ነፃና በ‘ቲሹ ካልቸር’ ድንች ለማምረት የሚያስችሉ፣ 800 የችግኝ ማባዣ ቋቶችን አዘጋጅቼያለሁ፡፡’’ ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 01/2012 ዓ.ም (አብመድ) በደቡብ ጎንደር ዞን ደጋማ አካባቢዎች የድንች ምርት በስፋት ይመረጣል፡፡ ከደቡብ ጎንደር ላይ ጋይንት ወረዳ ጎብጎብ ቀበሌ ያነጋገርናቸው አርሶ አደር አቶ ሙላት መለሰ የድንች ምርት ሕይወታችው ላይ ትልቅ ለውጥ እንዲያመጡ ያስቻለ መሆኑን ነግረውናል፡፡ ‘በለጠ’ የሚባል የድንች ዘር በብዛት እንደሚጠቀሙም ተናግረዋል፡፡ ምርቱ ግን በመጀመሪያ ዓመት ዘርተው ከተጠቀሙበት ጊዜ በኋላ በየዓመቱ እየቀነሰ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ ይህም ‘‘ዘሩ አርጅቷል’’ ነው ያሉት፡፡

በለጠ የተባለው የድንች ዘር መጀመሪያ እንደመጣ በሄክታር እስከ 200 ኩንታል ምርት ማገኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ግን በሄክታር እስከ 60 ኩንታል መቀነሱን ነው የሚናገሩት፡፡ ዩኒቨርሲቲው አዲስ የድንች ዘር ለማምጣት እየሠራ ያለውን የምርምር ሥራም ተሎ እንዲያደርስላቸውም ተናግረዋል፡፡ በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና የማኅበረሰብ አግልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት መንበሩ ተሾመ (ዶክተር) ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ሥራው በተጨማሪ ችግር ፈቺ የምርምር ሥራዎችን ለማቅርብ በእቅድ ይዞ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከስራዎች መካከልም ሀገረ-ገነት በሚገኘው የእርሻ ልማት ውስጥ ከበሽታ ነፃና በ‘ቲሹ ካልቸር’ ድንች ለማምረት የሚያስችሉ 800 የችግኝ ማባዣ ቋቶችን ማዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ ለሥራውም ከአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመነጋገር አስፈላጊ ግብዓቶች መቅርባቸውን ተናግረዋል፡፡
ከበሽታ ነፃ የሆነው የድንች ዘር ደግሞ በጥንቃቄ በምርምር ተሠርቶ ለአርሶ አደሮ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ ዓመት በመስኖ ለሚያለሙ አርሶ አደሮች የምርምር ውጤቱ እንደሚደርሳቸውም አስታውቀዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በደጋማ አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች በብዛት ድንች በማምረት መሰማራታቸውንና የምርት መጠኑ እየቀነሰ መምጣቱን በጥናት በማረጋገጥ ለምርምር ሥራ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል፡፡

በአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የቴክኖሎጂ ብዜት፣ ዘር ምርምር ዳይሬክተር እና የብሔራዊ የድንች ምርምር ፕሮግራም አስተባባሪ ሰመህኝ አስረዴ(ዶክተር) በክልሉ በምርምር ሥራ የተረጋገጡ ከ30 በላይ የድንች ዝርያዎች እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደሮች ግን ዳግም፣ በለጠ እና ጉድኔ የተባሉ የድንች ዝርያዎችን በብዛት እንደሚጠቀሙ ነው የተናገሩት፡፡ ከ10 ዓመት ወዲህ የመጣው ሥር አበስብስ በሽታ ደግሞ አርሶ አደርች በቂ የድንች ምርት እና ዘር እንዳያገኙ ማደርጉን ተናግረዋል፡፡ ‘‘በሽታውም በመሬት እስከ አራት ዓመት ስለሚቆይ አርሶ አደሮች በሚያመርቱት ምርት ቅናሽ ማሳየቱ የተረጋገጠ ነው’’ ብለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ አዴት ግብርና ምርምር ማዕከል፣ አማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ ደብር ታቦር ዩኒቨርሲቲ፣ ጉና ዩኔን እና ደሴ ቲሹ ካልቸር በቲሹ ካልቸር የወጡ አዲስ የድንች ዘሮችን ለአርሶ አደሮች ለማድርስ ‘ስክሪን ሃውስ’ በመሥራት የምርምር ሥራዎችን እየሠሩ እንደሆኑም አስታውቀዋል፡፡ እየተሠራ ያለው ‘ስክሪን ሃውሱ’ ነፍሳትንና በሽታን የማያስገባ ከበሽታ ነፃ የሆነ ዘር ለአርሶ አደሮች እንዲቀርብ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የድንች ዘር በስድስት ቫይረሶች ስለሚጠቃ በምርምር ተሻሽለው የሚቀርቡ የድንች ዘሮች አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉም አመላክተዋል፡፡ አርሶ አደሮች አሁን ከሚጠቀሟቸው የድንች ዘሮች መካከል ዳግም የተባለው የድንች ዘር ከሰባት ዓመት በፊት፣ በለጠ ከ11 ዓመት በፊት፣ ጉድኔ ከ15 ዓመት በፊት የተለቀቁ መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡ በኢትዮጵያ የመኽር ምርትን ሳይጨምር ከ296 ሺህ ሄክታር በላይ ድንች እንደሚዘራም ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ፎቶ፡- በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here