“የዲቾቶ ድንበር ተሻጋሪ የጭነት ተሽከርካሪዎች ተርሚናል ለጂቡቲና ኤርትራ ወደቦች አማካኝ ቦታ መገንባቱ ጉልህ ፋይዳ አለው” ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ

0
113
“የዲቾቶ ድንበር ተሻጋሪ የጭነት ተሽከርካሪዎች ተርሚናል ለጂቡቲና ኤርትራ ወደቦች አማካኝ ቦታ መገንባቱ ጉልህ ፋይዳ አለው” ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ
ባሕር ዳር፡ ጥር 13/2013 ዓ.ም (አብመድ) ለጂቡቲና ኤርትራ ወደቦች አማካኝ ቦታ የተገነባው በአፋር ክልል ‘የዲቾቶ ድንበር ተሻጋሪ የጭነት ተሽከርካሪዎች መቆያ ተርሚናል’ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንደሚኖረው የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ገለጹ።
በአፋር ክልል በ63 ሚሊየን ብር የተገነባው የዲቾቶ ድንበር ተሻጋሪ ተሽከርካሪዎች ተርሚናል የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ተመርቋል። በአፋር ክልል ዲቾቶ በሚባል አካባቢ ጋላፊ ከተማ አቅራቢያ ላይ የተገነባው የድንበር ተሻጋሪ የጭነት ተሽከርካሪዎች መቆያ ተርሚናል ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ተመርቋል።
የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በወቅቱ እንዳሉት፤ የድንበር ተሻጋሪ የጭነት ተሽከርካሪዎች መገንባቱ የኮሮናቫይረስን ከመከላከል ባሻገር አይነተ ብዙ ምጣኔ ሀብታዊ አበረክቶት ይኖረዋል።
ከ750 እስከ 800 ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ የሚችለው የዲቾቶ ተርሚናል ለድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች የንጽህና መጠበቂያ ክፍሎችና የኮሮናቫይረስ ምርምራ አገልግሎት መስጫዎች እንዳሉት ገልጸዋል።
ለጂቡቲና ኤርትራ ወደቦች አመቺ ስፍራ ላይ የተገነባው ተርሚናሉ በልማት ኮሪደሮች የሎጂስቲክስ ዘርፉን ለማሳለጥ፣ በወጭ ቅነሳና ለአካባቢው ማህበረሰብ ስራ እድል ፈጠራ የሚኖረው ምጣኔ ሃብታዊ ፋይዳው የጎላ እንደሚሆንም ገልጸዋል።
“ከዚህ ባሻገር በጂቡቲ ወደብ በወረፋ ሲቸገሩ የነበሩ አሽከርካሪዎች በተርሚናሉ ቆይተው ሳይጉላሉ እንዲስተናገዱ የሚያስችል ነው” ብለዋል። ይህም ለድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች እንግልትና ወጪን እንደሚቀንስ ተናግረዋል።
የመጀመሪያው ምዕራፍ የተርሚናሉ ግንባታ 63 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ወጭ እንደተደረገበት ተገልጿል።
ኢዜአ እንደዘገበው በቀጣይ ሁለት ምዕራፎች የሚገነቡ አገልግሎት መስጫና መሰረተ ልማቶችን ጨምሮ በአጠቃላይ የተርሚናል ፕሮጀክቱ 121 ሚሊዮን ብር ወጭ ይጠይቃል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here