የደቡብ ጎንደር ዞንና የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር የከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ኮንፈረንስ በደብረታቦር ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

20

ደብረታቦር፡ ግንቦት 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኮንፈረንሱን በንግግር የከፈቱት የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ኮንፈረንሱን ለማካሄድ ያስፈለገበት ምክንያት በተለያዩ ጊዜያት እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን በመወያየት መፍትሄ ለመስጠት መኾኑን ተናግረዋል፡፡

ጽንፈኝነት፣ ሥርዓት አልበኝነትና የማኀበራዊ ሚዲያ የተሳሳተ የትግል ስልት የክልላችን አሁናዊ ፈተናዎች ናቸው ያሉት አቶ ግዛቸው አምርሮ በመታገል ለክልሉ ሰላምና ለሕዝቡ አብሮነትና ተጠቃሚነት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡የኮንፈረንሱ አስተባባሪና የደቡብ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ ጥላሁን ደጀኔ የኮንፈረንሱ ዓላማ በክልላችንም ኾነ በሀገራችን የሚታየው ጽንፈኝነት ለሀገር ሠላም ጸር ስለኾነ ተወያይተን የጠራ አመለከካከት ለመገንባትና ወንድማማችነትን ለማስፈን፤ የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ኀብረተሰቡ በሠላም እንዲኖር ለማድረግ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አቶ ይርጋ ሲሳይ በወቅቱ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች በርካታ መኾናቸውን ጠቅሰው ለመፍትሄውም በውይይት ትክክለኛ አቋም ላይ በመድረስ መታገል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ”ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ሕዝባችን እናሻግር” በሚል መሪ መልዕክት የተጀመረው ኮንፈረንስ ለ3 ቀናት እንደሚቆይና በወቅታዊ ችግሮች ላይ በመወያየት ለመፍትሄዎቹም ቁርጠኛ ኾኖ ለመሥራት መግባባት ላይ እንደሚደረስ ተገልጿል፡፡

ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!