የደሴት ላይ ጥምቀት!

79
ነጭመደበኛ
ነጭመደበኛ
ባሕር ዳር: ጥር 10/2015 ዓ.ም (አሚኮ) “ውቢቷ” የሚል የመጠሪያ ካባ፤ የውበት ማማ የተደረበላት በውኃ ላይ የጸናች ተዓምረኛ ከተማ ናት፡፡ በዓለማችን ሽንጠ ረጅሙ የዓባይ ወንዝ መቀነቷ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በስፋቱ ተወዳዳሪ የማይገኝለት የተንጣለለው የጣና ሐይቅ ልባሷም ፤ሞገሷም ነው፡፡ በሕይዎት እና በምህረት ወንዝ፤ በጥልቅ እና ረቂቅ ሐይቅ የተከበበች ምስጢራዊ ከተማ ናት፤ ባሕር ዳር፡፡
በርካቶች ባሕር ዳር ስትነሳ ቀድሞ ወደ አዕምሯቸው የሚመጣው ውበቷ፣ ተስማሚነቷ እና ተናፋቂነቷ ነው፡፡ ባሕር ዳር ግን ከዓለማዊ ውበት፤ ከስጋዊ ምቾት የተሻገረች ቅዱስ ከተማም ነች ይላሉ አበው የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት፡፡ ከገነት በር እንዲፈስስ የታደለው የዓባይ ወንዝ ጎረቤቷ፤ ታሪክ እና ሃይማኖት፤ ቅርስ እና ማንነት፤ የከተመበት የጣና ሐይቅ ቤቷ ነው፤ ለውቢቷ ባሕር ዳር፡፡
ጥምቀትን በባሕር ዳር ማክበር ሃይማኖታዊ መሰረት እና ዓለማዊ ሃሴት አለው ያሉን በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የደብረ ቅዱሳን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ዋና አስተዳዳሪ መላከ ምሕረት ግሩም አለነ ናቸው፡፡ የጥምቀት በዓል የሰው ልጅ የዳነበት እና ውኃ የከበረበት በዓል ነው የሚሉት መላከ ምሕረት ግሩም፤ የሐይቅ ጎረቤት፤ የወንዝ ባለቤት በሆነችው እና በውሃ ላይ በጸናቸው ከተማ ጥምቀትን ማክበር ልዩ ትርጉም አለው ይላሉ፡፡
ጥምቀት ኢየሱስ ክርስቶስ በመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ በውኃ የተጠመቀበት በዓል መሆኑን በማንሳት “ጥምቀት ውኃ የከበረበት በዓል” ነው የሚሉት መላከ ምሕረት ግሩም፤ ውኃ የከበረበትን በዓል በውኃ በተከበበች ከተማ ማክበር ልዩ ትርጉም ይሰጣል ይላሉ፡፡
ውኃ ከበረ ሲባልም ኢየሱስ ክርስቶስ በማር እና ወተት፤ በወይን እና ዘይት መጠመቅ የሚችል አምላክ ሆኖ ሳለ እንደ ፀሐይና ጨረቃ፤ ክረምት እና በጋ ድሆች ሁሉ በቀላሉ ያገኙት ዘንድ “በውኃ ተጠመቀ” ሲሉ ያመሴጥሩታል፡፡
በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ውስጥ ከ50 የሚበልጡ አጥቢያዎች አሉ፡፡ እንደ ደብረ ማርያም እና መንበረ መንግሥት ቤዛዊት ማርያም ኹሉ በተለያየ ቦታዎች የጥምቀትን በዓል በተለየ መልኩ የሚያከብሩ አጥቢያዎች እንዳሉ የሚናገሩት መላከ ምሕረት ግሩም፤ በዋናነት በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ውስጥ የሚገኙ አጥቢያዎች በሁለት ባሕረ ጥምቀቶች የጥምቀትን በዓልን ያከብራሉ ብለዋል፡፡
ባሕረ ጥምቀቶቹ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያላቸው አምሳለ ዮርዳኖስ ናቸው የሚሉት መምህሩ የዓባይ ወንዝን እና የጣና ሐይቅን መሰረት አድርገው ጥምቀቱን የሚያገለግሉ ናቸው ብለውናል፡፡ አጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ የሚገኘው እና የዓባይ ወንዝን መሰረት ያደረገው ባሕረ ጥምቀት አንዱ ነው፡፡ ሌላኛው ግን ከረጂም ጊዜ በፊት ባሕር ዳር ከተማ ጥምቀተ ባሕርን ታስተናገድበት የነበረችው እና በቅርቡ እንደገና የተጀመረው ሽምብጥ ሚካኤል ገዳም አቅራቢያ በተለምዶ “ዲፖ” አካባቢ የሚገኘው ባሕረ ጥምቀት ነው፡፡
ዲፖ አካባቢ የሚገኘው ባሕረ ጥምቀት የጣና ሐይቅን መሰረት ያደረገ ጥምቀተ ባሕር ነው ያሉን መላከ ምሕረት ግሩም፤ ቀድሞ የጥምቀት በዓል የሚከበርበት ቢሆንም ለረጂም ጊዜ አገልግሎት ሳይሰጥ ቆይቶ ነበር ይላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አሥኪያጅ እና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ አብርሃም ልዩ ጥረት፤ በቅርቡ 40 ሺህ በላይ ካሬ ቦታ ሀገረ ስብከቱ ተቀብሎ የግንባታ ሥራው እየተፋጠነ ይገኛል፡፡ በሀገረ ስብከቱ የሚገኙ አድባራት እና ገዳማት ባሰባሰቡት ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ባሕረ ጥምቀቱን በተለየ መልኩ ለመሥራት እርብርብ እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡
ባሕር ዳር ለጥምቀት የተፈጠረች ከተማ ብቻ ሳትሆን በወንዝ እና ሃይቅ የተከበበች ገዳምም ናት የሚሉት መላከ ምሕረት ግሩም፤ የጥምቀትን በዓል በባሕር ዳር መታደም የጥምቀትን በዓል ሃይማኖታዊ ትርጉም መመርመርም ነው ብለውናል፡፡ እናም ጥምቀትን በባህር ዳር ተገኝታችሁ “የደሴት ላይ ጥምቀትን” ታደሙ የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!