የደረሱ ሰብሎች በዝናብ ጉዳት ሳይደርስባቸው ቀድሞ መሰብሰብ እንደሚገባ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አሳሰበ፡፡

0
182

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ዶክተር ሰሎሞን አሰፋ የሜቲዮሮሎጅን ትንበያ መሠረት አድርገው እንደገለጹት በቀጣይ በክልሉ ከፍተኛ የሆነ ዝናብ ስለሚኖር የደረሱ ሰብሎችን ቀድሞ መሰብሰብ ይገባል፡፡

በአማራ ክልል በ2011/2012 ምርት ዘመን በክልሉ የተሻለ ዝናብ ስርጭት ስለነበር በሰብል ላይ በሽታ አልተከሰተም፡፡ በተለይም ደግሞ እንደ ባቄላ፣ ሽምብራ፣ ምሥር እና የመሳሰሉ የጥራጥሬ ሰብሎች የተሻለ ቁመና ላይ እንደሚገኙ ነው ዶክተር ሰሎሞን የገለጹት፡፡

ይሁን እንጅ የሜቲዮሮሎጅ ትንበያ እንደሚያሳየው በቀጣይ ከፍተኛ የሆነ ዝናብ ስለሚኖር አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ መሰብስብ እንደሚገባው ዶክተር ሰሎሞን አሳስበዋል፡፡

ከሰበሰበ በኋላም በጎርፍ እንዳይጠቃ ከመሬት ከፍ በማድረግ ማከማቸት (መከመር) እና በቶሎ ወቅቶ ወደ ጎተራው ማስገባት እንደሚገባ ምክትል ቢሮ ኃላፊው አሳስበዋል፡፡ ባለሙያዎችም ማኅበረሰቡን በማንቃት የደረሱ ሰብሎች ጉዳት ሳይደርስባቸው እንዲሰበሰቡ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የአርሶ አደሩን ሕይወት መቀየር የሚቻለው በዝናብ ያልተበላሸ ጥራት ያለው ሰብል ለምግብነት እና ለገበያ ሲቀርብ እና አርሶ አደሩም ባቀረበው ምርት የተሻለ ዋጋ ሲያገኝ ነው፡፡ አርሶ አደሩ የለፋበትን ምርት ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ጉዳት እንዳይደርስበት በወቅቱ እንዲሰበሰብ የሁሉም ድርሻ መሆን ይገባዋል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሰራ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here