የዚያ ዘመን ቅርሶች በዚህ ዘመን መጥፋት የለባቸውም!

0
33
የዚያ ዘመን ቅርሶች በዚህ ዘመን መጥፋት የለባቸውም!
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 22/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ጥበብ ጸንሳ ጠቢባንን የወለደች፣ በጠቢባን ተገንብታ የከበረች፣ በራሷ ፊደል ከትባ ያስነበበች፣ ትንቢት የተነገረባት፤ ተነግሮ የማያልቅ፣ ተሰምቶ የማይጠገብ ታሪክ ያላትና የረጅም ዘመናት የሀገረ መንግሥት ምስረታ ታሪክ ያላት ምስጢራዊት ምድር ናት፡፡ ተፈጥሮ የለገሳት ገጸ በረከት፣ ከዘመኑ የቀደመ የጥበብ አሻራ ያረፈባቸው ኪነ ህንፃና ሌሎች ሰው ሠራሽ ቅርሶች ባለቤትም ናት፡፡ኢትዮጵያ!
ጥበብን ከመንፈሳዊ ሕይወት ያሰናሰለው የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስትያን፣ የኢትዮጵያዊነት ውል ላይፈታ የተቋጠረበት የጎንደር ቤተ መንግሥት፤ የፍቅር ሸማ የተፈተለበት የጀጎል ግንብ፤ ኢትዮጵያ ከፍ ብላ የተደመጠችበት አንኮበር ቤተ መንግሥት፤ ፍቅር፣ አንድነት መተሳሰብና መረዳዳት የተሰበከበት አይጠየፍ አዳራሽ፣ የአክሱም ሐውልት፤ የጢያ ትክል ድንጋይ፣ የሶፍ ኡመር ዋሻና ሌሎች ሠው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ቅርሶች ለዚህ ሕያው ምስክሮች ናቸው፡፡ በአማራ ክልል ብቻ ከ4 ሺህ በላይ ቋሚና ከ130 ሺህ በላይ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች እንዳሉ ይታወቃል፤ በክርስትናም ሆነ በእስልምና ሃይማኖቶች ሚስጥራት የያዙ ቅዱሳን መጻሕፍትና ሌሎች የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ፣ ተንቀሳቃሽና ቋሚ ቅርሶችም በስፋት የሚገኙበት ክልል ነው፡፡
May be an image of outdoorsየስልጣኔ አሻራ ያረፈባቸውና የኢትዮጵያ ክብር መሠረቶች፣ የአማራ ክልል ሕዝብ መገለጫ የኾኑ ጥንታዊና ታሪካዊ ቅርሶች አሁን ላይ የመፍረስ አደጋ ተጋርጦባቸዋል፡፡ እንደየሁኔታው የሚለያይ ቢሆንም ቅርሶች ተገቢ እንክብካቤ አለማግኘታቸው፣ ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አናሳ መኾን፣ የቅርሶች እድሜ እየገፋ መሄድ፣ ቅርስን መንከባከብ የመንግሥት ኀላፊነት ብቻ አድርጎ መመልከት እንደ ምክንያት ይነሳሉ፡፡ በዚህም ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶቹ የኅልውና አደጋ ላይ ወድቀዋል፡፡ በሌላ በኩል በሕልውና ፈተና ውስጥ የወደቁትን ለመጠገን፣ ለመንከባከብና መዳረሻዎችን ለማልማት የአቅም ችግር አጋጥሟል፡፡
በመንግስት በጀት ብቻ በክልሉ ያሉ ቅርሶችን ከጉዳት መታደግ ስለማይቻል የክልሉ መንግሥት ችግሩን ለመቀነስ የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ፈንድ ጽሕፈት ቤት አቋቁሞ እየሠራ ነው፡፡ ይህም የኅብረተሰቡን ተሳትፎ ያሳድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው የጽሕፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጁ የሺዋስ ደሳለኝ የተናገሩት፡፡ የጽሕፈት ቤቱ የሥራ ድርሻ ለቅርስ ጥገና የሚውል ሀብት ማሰባሰብ ነው፤ የባሕልና ቱሪዝም መዋቅሩ ደግሞ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ቅርሶችን በመለየት እንዲታደሱ ያደርጋል፡፡
ጽህፈት ቤቱ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ከልዩ ልዩ የኅብረሰተብ ክፍሎች፣ በቱሪዝም አገልግሎት ከሚጠቀሙ ተቋማት፣ ከክልሉ መንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ የቱሪዝም መዳረሻዎች ከሚያገኙት የቱሪዝም ገቢና ሌሎች ዘዴዎችን ተጠቅሞ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ በተለይ በመንግሥት ይዞታ ሥር የነበሩ የቱሪዝም መዳረሻዎች የሚያገኙት ገቢ ወደ ተቋሙ እንዲገባ በማድረግ ለከፋ ችግር የተጋለጡ ቅርሶች እንዲጠገኑ ተደርጓል፡፡ ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ የባሕልና ቱሪዝም ተቋሟት ሠራተኞች ከደመወዛቸው ድጋፍ እንዲያደርጉም እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ልዩ ልዩ ሁነቶችን በማዘጋጀት ቅርሶችን በተሻለ መንገድ ከጥፋት ለመታደግም ታቅዷል፡፡
ምንም እንኳን ከ2012 ዓ.ም አጋማሽ ወዲህ መዳከም ቢታይም ከተሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ ከ6 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም ለጎንደር ቤተ መንግሥት፣ ለደሴ ጥንታዊ ሙዚዬም፣ ለጢስ ዓባይ የቱሪዝም መዳረሻ ማዕከል፣ ለዳጋ እስጢፋኖስ፣ በሰሜን ሸዋ ዞን ለሚገኘው ለሣኅለስላሴ ቤተመንግሥት እና ለአሸተን ማርያም ቤተክርስቲያን ጥገና መደረጉን ተናግረዋል፡፡
አማራ ክልል የበርካታ ቅርሶች መገኛ መኾኑ ይታወቃል፡፡ ታሪክን እና ቅርስን ተንከባክቦ ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመኾን፤ ለተተኪ ትውልድም ለማስተላለፍ የተጋረጡ የሕልውና አደጋዎችን ማስወገድ ግድ ይላል፡፡ በሀገሪቱ ዋና የኢኮኖሚ ምሶሶ ተብለው ከተለዩት መካከል አንዱ የቱሪዝም ዘርፉ ነው፡፡ ይሕም ለዘርፉ ትኩረት እንዲሰጠው የሚያደርግ ነው፡፡ ይኹን እንጂ የማኅበረሰቡ ተሳትፎ ከሌለ ውጤታማነቱ አጠያያቂ ይኾናል፡፡
ቅርስ በሀይማኖትና በዘር ወይንም በሌላ የሚወከል አይደለም፤ የሰው ልጅ አሻራ ያረፈበት የማንነት መገለጫ እንጂ፡፡ ቀደምት አባቶች ሠርተው፣ ተንከባክበውና ጠብቀው ያስረከቡትን የስልጣኔ አሻራዎች እንዳይጠፉ የአሁኑ ትውልድ ኀላፊነት አለበት፡፡ መገናኛ ብዙኃንም በቅርሶች ላይ የደረሰውን የሕልውና ፈተና ማሳወቅ አለባቸው፡፡
ኢትዮጵያ ታሪክ እንዲኖራት፣ ዓለም አቀፍ እውቅና እንድታገኝ እና ማንነቷ እዲገለጥ ያደረጓት ቅርሶች ትውልዱ እስካሁን ለደረሰበት ደረጃ ዋልታና ማገር ናቸው፡፡ ወደፊትም ትልቅ ትሩፋት አላቸውና ትውልዱ በጥንቃቄ ሊንከባከባቸው ይገባል፡፡ አቶ የሺዋስ ያሉትም ይህንኑ ነው፡፡ ተቋሙ ተደራጅቶ ሥራ መጀመሩ በራሱ ግብ አይኾንም፤ ሰዎች የማንነታቸው መገለጫ የኾኑትን ቅርሶች ለመጠበቅ አሻራቸውን ማሳረፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በገንዘብ፣ ችግሩን ለዓለም በማስተዋወቅ፣ በዕውቀትና በሀሳብ እገዛ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here