ባሕርዳር: የካቲት 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሙሉዓለም የባሕል ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ገብረማርያም ይርጋ 127ኛው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ስናከብር ለጥቁር ሕዝቦች ብርሃን የፈነጠቀበት መኾኑን እያሰብን ነው ብለዋል።
የዓድዋ ድል የሚነግረን ስክነትን፣ ብስለትን፣ ማስተዋልን፣ ጀግንነትንና ታሪክን የማስቀጠል ትሩፋትን ነው ብለዋል። በዓድዋ ታሪክ ይነበባል፣ ጀግንነት ይቀዳል፣ በራስ አቅም ችግርን የመፍታት ችሎታን እንመለከትበታለን ነው ያሉት። ዓድዋ ተነግሮ የማያልቀውን ታሪክ የምንመለከትበት የድል ጮራችን ነውም ብለዋል።
ዓድዋ መደማመጥን፣ መግባባትን፣ መተባበርን እና መስማማትን የተመለከትንበት የአባቶቻችንን የብስለት ደረጃ ያየንበት ክስተት መኾኑን ነዉ የተናገሩት። ከትናንት አባቶች የወረስነውን ሀገር የማስቀጠል እሳቤ የሚነግስበት ደማቅ ታሪክ ነው ብለዋል። በራስ ታሪክ የመኩራት፤ በነጮች መወረር የማይገባን ሕዝቦች መኾናችን ያሳየንበት ነው። በአሁኑ ሰዓት ያሉ ወጣቶች ከታሪክ ጀግንነትን ቀድተው ሀገር የማሻገር ኀላፊነት አለብን ለዚህ ሁላችንም የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል።
ለዓድዋ ድል መገኘት ትልቁን ድርሻ እምዬ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ ይወስዳሉ ቀሪው በዘመኑ ለነበሩ የጦር አዛዦች እና ሹማምንት እንዲሁም ሀገሬን አላስደፍርም ላለው መላው ሕዝብ ነው ብለዋል።
ሌላው በመታሰቢያ በዓሉ ላይ ያገኘናቸው አርበኛ ወርቁ አስማረ ሀገርን መጠበቅ ከአባቶቻቸው የወረሱት እና ለልጆቻቸው የሚያስረክቡት መኾኑን ተናግረዋል። አርበኛ ወርቁ አስማረ ኢትዮጵያ በጠላት በተወረረችበት ወቅት ካራማራ መዝመታቸዉን እና በድል መመለሳቸውን ነግረውናል። አምስት ልጆች ወልደው ወታደር አድርገዋል። አርበኛ ወርቁ ታጥቆ ሀገርን መጠበቅ ከአባቶቻቸው የወረሱት እንደኾነ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን ማወቅ ላላወቀው ማሳወቅ የእኛ የአባቶች ተግባር መኾን አለበትም ብለዋል።
ቀጣይ ኢትዮጵያ አድጋ እና በልጽጋ ዜጎች ያለ ነቀፋ እና መሸማቀቅ የሚኖሩባት ለማድረግ የራሳቸወን ኀላፊነት እንደሚወጡም ተናግረዋል። የአሁኑ ትውልድ ሀገር ስትወረር ማቄን ጨርቄን ሳይል ለሀገሩ ዘብ እንዲቆም ፣ያለ ሀገር አንድ ቀን እንኳን መኖር፣ መደሰት እንደማይችል አውቆ ሀገሩን ከወራሪ እንዲጠብቃት ጥሪ አስተላልፈዋል። አርበኛ ወርቁ ሀገርን መጠበቅ ከአባቶቻቸው የወረሱት እና ለልጆቻቸው የሚያስረክቡት ደብቀው የማያስቀሩት ሀሳብ መኾኑን ተናግረዋል።
በሙሉ ዓለም የባሕል ማዕከል ተዋናይ አመለ ወርቁ የአባቶቹን ታሪክ ለመድገም ሰንደቅ አላማ መቀበሉን ነግሮናል። ሰንደቅ አላማው የፍቅር፣ የጀግንነት እና የአንድነት ማሳያ ነው ብሎናል። የአባቶቻችንን ታሪክ ተቀብየ ከፍ ያለች ኢትዮጵያን ለመጭው ትውልድ ለማስረከብ ጠንክሬ እሠራለሁ፣ በተሠማራሁበት የሙያ ዘርፍም ሀገሬን በተገለጠችበት ልክ ለትውልዱ አስተላልፋለሁ ብሎናል።
ሀገራችን አንድነቷ ተጠብቆ፣ ሰላሟ ተረጋግጦ በኢኮኖሚ ዳብራ ለትውልድ የምትሻገርበትን መንገድ አመቻቻለሁ ብሎናል።
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!