የዓለም ጭቁን ሕዝብ ድምጽ!

0
144

ባሕር ዳር: የካቲት 06/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአጠቃቀም ቅለቱ፣ ድምበር አልባ ስርጭቱ፣ ለአያያዝ መመቸቱ፣ ምጣኔ ሃብታዊ ተደራሽነቱ፣ ምስል ከሳችነቱ እና በብቸኝነት ወቅት ጓደኝነቱ በበርካቶች ዘንድ ዘመን አይሽሬ ተመራጭ የመረጃ ምንጭ ያደርገዋል። ፍቅር ከጽናፍ ዓለም እስከ አጽናፍ ዓለም ተዘርቶበታል፣ ጀግና ተወድሶበታል፣ ጀግንነት ተሰብኮበታል፣ አብዮት ተለኩሶበታል፣ ርእዮተ ዓለም ተቀንቅኖበታል፣ የሰው ልጅ ማንነት ተነግሮበታል፣ ፈጠራ ተዋውቆበታል፣ የሰላም ነጋሪት ተጎስሞበታል፣ እድገት ተተልሞበታል፣ ተሞክሮ ተቀምሮበታል የዓለም ጭቁን ሕዝብ ድምጽ በሆነው ራዲዮ።
ዓለም እንደዛሬው መንደር ሳትሆን የዓለም ሕዝብን በማቀራረብ እንደ ራዲዮ ባለውለታ ያለ አይመስልም። የሰው ልጅ እንደዛሬው በመረጃ ምንጮች ሳይከበብ እና በመረጃ ሳይጥለቀለቅ ራዲዮ ወሬ ነጋሪ ድልን አብሳሪ ሆኖ አገልግሏል። የታፈኑ ድምጾች መተንፈሻ፣ የዲሞክራሲ እሳቤ መጎልመሻ እና የፍትህ ጉባኤ መዳረሻ ራዲዮ ነበር ይባላል። ምድሪቱ እንደዛሬው በሃሰት መረጃ ሳትናጥ፣ በተዛባ መረጃ ሳትንቀጠቀጥ እና በመረጃ ብክለት ሳትናወጥ ራዲዮ እስትንፋሱ እንደፈጣሪ ፈዋሽ ነበር። ራዲዮ ለዓለም ጭቁን ሕዝብ የጆሮ ቀለብ ብቻ ሳይሆን የትግል መሳሪያም ነበር።
ራዲዮ ለዓለም ጭቁን ሕዝብ የጨለማው ዘመን ብርሃን፣ የጭቆናው ዘመን ድምጽ እና የፈተና ዘመን መውጫ መሰላል ሆኖ ማገልገሉን ታሪክ ይነግረናል። በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) አባል ሀገራት እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ስሌት 2011 ላይ የራዲዮ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲከበር ሃሳብ ቀረበ። በ2012 (እ.አ.አ) በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይም የካቲት 6 ቀን (ፌብሪዋሪ 13) በየዓመቱ የራዲዮ ቀን ሆኖ እንዲከበር ስምምነት ላይ ተደረሰ።
ራዲዮ የዓለምን የድህነት ሸክም ካቃለሉ እና የጭቆና ቀንበርን ከገፈፉ የብዙኀን መገናኛ መሳሪያዎች መካከል ግንባር ቀደም ተደርጎ ይወሰዳል። ራዲዮ የዓለም አመለካከትን የቀየረ፣ እይታን የዘወረ፣ አስተሳሰብን ያዘመነ፣ የጋራ መግባባቶችን የፈጠረ እና እድገትን ያሸጋገረ የመገናኛ ዘርፍ በመሆኑ በየዓመቱ መዘከሩ ተገቢ ነው የሚሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ብዙ ናቸው።
በባሕር ዳር ዮኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት እና ሥነ ተግባቦት ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ጀማል ሙሃመድ (ዶክተር) አንድ ወቅት ስለራዲዮ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እና አበርክቶ ሲገልጹ “በድህነት ዓለም እና በጭቆና ቀንበር ውስጥ ላለፉ የዓለም ሕዝቦች የራዲዮ ውለታ እጅግ ከፍተኛ ነው” ነበር ያሉት። ዓለም አሁን ለደረሰችበት በርካታ አማራጭ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች ስርጭት ራዲዮ እርሾ ቢኖረውም እየተፈጠረ ላለው የሃሰት መረጃ ስርጭት የራዲዮ ተደራሽነት ተገቢውን ትኩረት አለመሰጠት ምክንያት ሆኗል ይላሉ ዶክተር ጀማል። በገጠር እና በከተማ፤ በተማረው እና ባልተማረው መካከል ያለው የመረጃ ስርጭት ያልተመጣጠነ እና የራዲዮ ተደራሽነት አሁንም ውስንነቶች ያሉበት መሆኑን እንደማሳያዎች በማንሳት።
በኢትዮጵያ የራዲዮ ስርጭት እና አገልግሎትን አስመልክቶ የተለያዩ የመረጃ ምንጮች የተለያዩ ግን ደግሞ የተቀራረቡ ጊዜያቶችን ያነሳሉ። ጋዜጠኛ መዝሙር ሐዋዝ “የብዙሃን መገናኛ እድገት በኢትዮጵያ” በሚል ርእስ ባሳተሙት መጽሐፋቸው የራዲዮ ጣቢያ ለማቋቋም በ1923 ዓ.ም በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ አካበቢ የመሠረት ድንጋይ መጣሉን ይነግሩናል። ከዓመታት የግንባታ ሂደት በኋላም መስከረም 2/1928 ዓ.ም በወቅቱ የሀገሪቱ መሪ የነበሩት ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ባደረጉት ንግግር ታሪካዊ ስርጭቱን ጀምሯል ይላሉ።
ግብርና የምጣኔ ሃብቷ መሠረት እና አርሶ አደር የሀገሪቱ ዋልታ በሆነባት ኢትዮጵያ የራዲዮ ጥቅም ቀላል የሚባል አይደለም። ልሳነ ብዙዋ ኢትዮጵያ፣ የታሪክና ታሪካዊ ቦታዎች ማህጸን የሆነችው ኢትዮጵያ፣ ቱባ ባህል እና የበዛ እምነት ባለቤቷ ኢትዮጵያ፣ ሰፊ የቆዳ ስፋትና የተለያየ መልካ ምድራዊ አቀማመጥ የተቸራት ኢትዮጵያ፣ የተለያየ ፖለቲካዊ እሳቤ እና ዘርፈ ብዙ ማሕበራዊ መስተጋብሮች የሚስተናገዱባት ኢትዮጵያ፣ በተዛባ እና በሃሰተኛ መረጃና የመረጃ ምንጮች የምትፈተነዋ የዛሬዋ ኢትዮጵያ እንደ ራዲዮ ላሉ ታማኝ የብዙሃን መገናኛ መረጃ ምንጮች የሰጠችው ትኩረት መጣኝ አይደለም የሚሉ የዘርፉ ምሁራን እና ባለሙያዎች አያሌ ናቸው።
የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የራዲዮ ቀን “ራዲዮ እና ተዓማኔነት” በሚል መሪ ሃሳብ ለ11ኛ ጊዜ ይከበራል። በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ዓለም የራዲዮ ቀንን ሲያከብር መንግሥታት፣ የዘርፉ የምርምር ተቋማት፣ ባለሙያዎች እና ተጠቃሚዎች ለሙያዊ ገለልተኛነትና ጥራት፣ ተደራሽን ለማክበር እና ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ አበክረው ሊሰሩ ይገባል ሲል ምክረ ሃሳቦቹን ያስቀምጣል።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/