የውጭ ኃይሎች ድጋፍ አሸባሪው ትህነግ ለዳግም ጦርነት እንዲነሳ ምክንያት መሆኑን ላውረንስ ፍሪማን ተናገሩ፡፡

133
ነጭመደበኛ
ነጭመደበኛ

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 23/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአሸባሪው ትህነግ ዳግም ወረራ ጉልበቱ እና ምክንያቱ በቀጣናው እና ከቀጣናው ውጭ ያሉ ጸረ-ኢትዮጵያ አቋም ያላቸው ኀይሎች ድጋፍ መሆኑን እውቁ አሜሪካዊ የአፍሪካ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኝ ላውረንስ ፍሪማን ገልጸዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ ለሦስተኛ ጊዜ በአማራ እና አፋር ክልሎች አካባቢ ይፋዊ ወረራ መጀመሩን ያወሱት ተንታኙ በቢሶበር፣ ዞብል እና ተኩለሽ አውዳሚ ጦርነት እየፈጸመ ነው ብለዋል፡፡
በቀጣናው እና ከቀጣናው ውጭ ያሉ ኀይሎች የሽብር ቡድኑን በበርካታ መንገድ እንደሚደግፉ ግልጽ ነው ያሉት ሚስተር ፍሪማን የሰላም አማራጮች በቀረቡበት በዚህ ወቅት የጦርነት ነጋሪት መጎሰሙ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
የአህጉሪቷ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኙ የሽብር ቡድኑ ትህነግ የውጭ ኀይሎች ድጋፍ እና ግፊት ባይታከልበት ምንም ዓይነት አዲስ ጦርነት የመቀስቀስ አቅም እንደሌለው ማረጋገጥ ቀላል ነው ብለዋል፡፡
ምክንያቱም የላኪዎቹ ግፊት የቀረቡለትን የሰላም አማራጮች ወደ ጎን በመተው እልቂት ወደ ሚያስከትል ዳግም ጦርነት ለመግባት አስገድዶታል ነው የሚሉት፡፡ አሸባሪው ትህነግ የፈረሰች ኢትዮጵያን የማየት ዓላማ ያለው ድርጅት መሆኑ ግልጽ ቢሆንም የተላላኪነት ሥራው የሚያስከፍለው ዋጋ ከባድ እንደሆነም ተንታኙ አብራርተዋል፡፡
የአሸባሪውን ትህነግ እኩይ ዓላማ የሚደግፉ ብሎም የሚገፋፉት የውጭ ኃይሎች አሉ ያሉት ሚስተር ፍሪማን ይህ አደገኛ አካሄድ በመሆኑ ከድርጊታቸው የማይታቀቡ ከሆነ የሚከተለው አደጋ ቀጣናዊ እና አህጉራዊ ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡
ለአፍሪካ ሰላም የሚሰሠሩ ኃይሎች እና ሀገራት ካሉ አሸባሪው ትህነግ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠን መንግሥት ለመውጋት እና ሀገር ለማፍረስ የጀመረውን ጦርነት ሊያወግዙ ይገባል ብለዋል፡፡
ለሽብር ቡድኑ የሚደረገውን የውጭ ድጋፍ በተጨባጭ የሚታይ መሆኑን የጠቀሱት ሚስተር ፍሪማን ሰሞኑን ከኢትዮጵያ መንግሥት እውቅና ውጭ መነሻው ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የሆነ እና የጦር መሳሪያ እንደጫነ የሚገመት ወደ ትግራይ ሊገባ የነበረ አውሮፕላን በጀግኖቹ የኢትዮጵያ አየር ኃይል መመታቱን ለአብነት አንስተዋል፡፡ ለሽብር ቡድኑ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ለማድረግ የሚሞክሩ ቡድኖችም የኢትዮጵያ የምንጊዜም ጠላቶች ናቸው ብለዋል፡፡
ሚስተር ፍሪማን ለሽብር ቡድኑ የሚደረገው ድጋፍ ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተቋረጠ ግጭት እና ጦርነት እንዲኖር የሚፈልጉ የውጭ ኃይሎች እንዳሉ ማረጋገጫ ነው ብለዋል፡፡ ይህም የሀገሪቱን ማዕከላዊ መንግሥት ለማዳከም የሚደረግ ጥረት አንዱ አካል ነው ብለዋል ሚስተር ፍሪማን በማብራሪያቸው፡፡
ከጦርነቱ ጀርባ ያለው እውነት አንዲት እና ጠንካራ ኢትዮጵያ እንዳትኖር የሚደረግ ጥረት ነው ያሉት ሚስተር ፍሪማን ይህንን እቅድ ለማሳካት ብሔር ተኮር ግጭቶች በተደጋጋሚ ሲከሰቱ እንደነበር አውስተዋል፡፡ ለዚህም በተደጋጋሚ ሲከሰቱ ከነበሩት ብሔርን እና ሃይማኖትን መሰረት ካደረጉ ግጭቶች ጀርባ የሽብር ቡድኑ የሴራ እጆች ነበሩበት ብለዋል፡፡
ትልቁ ጥያቄ አሸባሪው ትህነግ እስካሁን ድረስ ለምን ጦርነትን ምርጫው አደረገ? የሚለው ነው ያሉት የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኙ ይህ አደገኛ፣ በየትኛውም ሁኔታ ተቀባይነት የሌለው አካሄድ ነው ብለዋል፡፡ ሚስተር ፍሪማን በማጠቃለያቸው ዓለም ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም የሽብር ቡድኑን የጦርነት ምርጫ ማውገዝ ይኖርበታል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J