የዋግኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የሻደይ በዓልን በድምቀት ለማክበር መዘጋጀቱን ገለጸ።

0
142

ሰቆጣ: ሐምሌ 24/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የዋግኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የሻደይ በዓልን በሰቆጣ ከተማ በድምቀት ለማክበር መዘጋጀቱን የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ስቡህ ገበያው ገልፀዋል።

የሻደይ በዓል ባለፉት ሁለት ዓመታት በኮሮና ወረርሽኝና በጦርነት በአደባባይ ሳይከበር ማለፉ የሚታወስ ነው ብለዋል።

“ሻደይ ኢትዮጵያ በግምባር ለድል፣ ለአንድነትና ለክብር” የበዓሉ መሪ ቃል ነው። ለዚህ ደግሞ መሰረታዊ ምክንያት በችግር ያሳለፈውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመፍረስ የታደገው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሕዝቡን ነፃ አውጥቶ አሁን አብሮ እየኖረ በመሆኑና ሠራዊቱ ግምባር ላይ ሆኖ ለ2 ዓመታት የተዳፈነውን በዓል ከዋግ ሕዝብ ጋር በጋራ የሚያከብሩት በመሆኑ ነው ብለዋል አቶ ስቡህ።

የዘንድሮው በዓል ከክልል አልፎ በኢትዮጵያዊ ቅርፅ እንደሚከበር ነው የገለፁት።

የሻደይ በዓል ሴቶች ከማጀት ወጥተው በአደባባይ በነፃነት የሚጫወቱበት የነፃነት ቀናቸው ነው። ይህ ደግሞ አንዱ የዲሞክራሲ ማሳያ ነው። በዓሉ ለሺህ ዓመታት ከማኅበረሰቡ ጋር ተቆራኝቶ የኖረ መሆኑንም ገልጸዋል።

የዘንድሮው በዓል በዞኑ ከነሐሴ 16 እስከ 21 የሚከበር ሲሆን ህፃናት፣ ልጃገረዶችና እናቶች በአደባባይ ከሚጫወቱት ትርኢት በተጨማሪ በሲምፖዚየም፣ በፓናል ውይይትና የዋግን ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ገፅታ በመጎብኘት እንደሚከበር ተናግረዋል።

በአፄ ካሌብ ዘመነ መንግሥት በታነፀው ውቅር መስቀለ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ውስጥ መግለጫውን የሰጡት አስተዳዳሪው ለዚህ ምክንያቱም ይህ ቅርስ በላል ይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ቅርፅ የታነፀ ቢሆንም ብዙ ኢትዮጵያውያን ይህን የራሳቸውን ታሪካዊ ቅርስ ስለማያውቁት በበዓሉ ለጉብኝት ዝግጁ መሆኑንም ለማሳወቅ ታሳቢ በማድረግ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያውያን በዕለቱ ተገኝተው የበዓሉ ታዳሚ እንዲሆኑና ዋግኽምራን እንዲጎበኙ የአስተዳደሩ አስተዳዳሪ አቶ ስቡህ ገበያው ጥሪ አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ:–ካሳሁን ኃይለሚካኤል

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/