የወልድያና አካባቢው ተወላጆች ለሆስፒታሉ ከ7 መቶ ሺህ ብር በላይ የሚያወጡ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ፡፡

0
103

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 27/2012 ዓ.ም (አብመድ) በውጭ አገራት የሚኖሩ የወልድያና አካባቢው ተወላጆች ለወልድያ ጠቅላላ ሆስፒታል ከ7 መቶ ሺህ ብር በላይ የሚያወጡ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል፡፡

በሳዑዲ አረቢያ የሚኖሩ የወልድያ፣ የሀብሩ፣ የጉባላፍቶ እና የቆቦ ከተማ ተወላጆች ለወልድያ ጠቅላላ ሆስፒታል ከ6 መቶ 40 ሺህ ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የህክምና ቁሳቁስ ዛሬ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ በአሜሪካ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ትብብር ደግሞ በ102 ሺህ ብር የተገዛ የሙቀት መለኪያ (ኢንፍራሬድ ቴርሞ ሜትር) ለሆስፒታሉ አስረክቧል፡፡

የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍስሐ የኋላ በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ድጋፉ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የሚያዙ ሰዎችን ለማከም፣ ለቀጣይም በሆስፒታሉ ያለውን የህክምና አገልግሎት ለማሳደግ እንደሚያግዝ አስረድተዋል፡፡

ሆስፒታሉ የህክምና ቁሳቁስ እጥረት እንዳለበት የገለጹት አቶ ፍስሐ ዛሬ የተረከቧቸው ድጋፎች በአገልግሎት ብዛት ተበላሽተው መሥራት ያቆሙትን መሳሪያዎች የሚተኩና እጥረቱንም የሚያቃልሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የወልድያ ከተማ ከንቲባ ሙሃመድ ያሲን በበኩላቸው ከዚህ በፊት በአሜሪካና በካናዳ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ለሆስፒታሉ 4 መቶ ሺህ ብር የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡

በውጭ ሀገራት የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ካላቸው ቀንሰው ወገናቸውን ለመደገፍ ሲልኩ ኅብረተሰቡ ደግሞ ራሱን እና ቤተሰቡን ከኮሮና ቫይረስ ሊጠብቅና ሆስፒታሉንም ሊያጠናክር እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ባለ ዓለምዬ-ከወልድያ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here