የኮመር ሥር ሽምግልና!

392

ባሕር ዳር: ሰኔ 19/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ባሕላዊ የሽምግልና ሥርዓት በየአካባቢው የሚከሰቱ አለመግባባቶችን እና ቅራኔዎችን በመፍታት አካባቢው ወደ ቀደመ ሰላሙ እንዲመለስ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የባሕል ጥናት (ፎክሎር) መምሕር ዶክተር ሞገስ ሚካኤል ከዚሕ በፊት ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ባሕላዊ የሽምግልና ተቋማት በኢትዮጵያ የቀደመ ታሪክ ያላቸው፣ በማኅበረሰቡ ሃይማኖታዊ እና መሰረታዊ እሴቶች ላይ የቆሙ በመኾናቸው በተገልጋዮች ዘንድ የሚታመኑ መኾናቸውን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ እንደ ዶክተር ሞገስ ገለጻ ተቋማቱ የጸጥታ ችግሮች ሲፈጠሩ በማብረድ፣ የግጭቶችን መነሻ ቀድሞ በመለየት እና በመከላከል ሚናቸው የጎላ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ዘመናዊ የፍትሕ ሥርዓት በቀላሉ ተደራሽ ባልኾነባቸው ገጠራማው የሀገሪቱ ክፍል ሰላምን በማስፈን የማይተካ ሚና እንደነበራቸው ገልጸዋል፡፡

ሀገር በቀል ተቋማቱ በሕቡዕ ተፈጽመው በመደበኛ ፍትሕ ሥርዓቱ መፍትሔ ያላገኙ ችግሮችን ጭምር በማሕላ ባሕላዊ መንገዶች በመለየት አጥፊውን በመቅጣት እና ተበዳዩን በመካስ ሚናቸው የጎላ ነው፡፡

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ኪንፋዝ በገላ ወረዳ በአንዲት የኮመር ዛፍ ሥር በተደረገው የሽምግልና ስርዓት ላይ በመገኘት ባሕላዊ ሽምግልናው ምን ያሕል ችግር ፈች እንደኾነ ችግር ያጋጠማቸውን ወገኖች እና የሀገር ሽማግሌዎችን አነጋግረናል።

“ኮመር” ቆምጣጣ ፍሬ የሚያፈራ ዛፍ ሲኾን ፍሬው በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ ለኾድ ህመም እንደ ፍቱን መድሃኒት ተደርጎ ይወሰዳል። ዛፉ ለአከባቢው ሰው እና እንስሳት ጥላም ነው። የሀገር ሽማግሌዎች የችሎት ማስኬጃ ሆኖ እያገለገለ ነው።

ቀደም ባሉት ጊዜያት የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች በወረዳው የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት የሽምግልና ሥርዓት የሚያካሂዱት ለተሸማጋይ ወገኖች እንደ አማካይ ተደርጎ በሚወሰደው ከዚህ የዛፍ ጥላ ሥር በመሰባሰብ ነበር። አኹን ላይም የሀገር ሽማግሌዎች በዚህ የኮመር ዛፍ ሥር ተገናኝተው ዕለታዊ ግጭቶችን ቀድሞ በመፍታት ለአካባቢው ሰላም መስፈን አባታዊ ግዴታቸውን እየተወጡ ነበር ያገኘናቸው።

በዚህም የአካባቢው ማኅበረሰብ በዛፏ ፍሬ ከሕመሙ፣ ከጥላዋ ሥር በመሰባሰብ ደግሞ ከችግሮቹ እየተፈወሰ ይገኛል።

በሽምግልና ሥርዓት ችግሮቻቸው ከተፈታላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ምትኩ ተላከ ይገኝበታል። ወጣት ምትኩ በተፈጠረ ግርግር ምክንያት አንድ ግለሰብ በጥይት ይጎዳበታል። ቤተሰቦቻቸውም በመደናገጥ የሚያደርጉት ጠፋባቸው። በዚህን ጊዜ ነበር የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች ችግሩ እንደተፈጠረ ቀድመው በኮመሯ ሥር በመሰባሰብ በመጀመሪያ የማረጋጋት ሥራ የሠሩት። በመቀጠል ሁለቱን ወገኖች በማገናኘት እርቅ መፈጸሙን ወጣቱ ነው የነገረን። በሀገር ሽማግሌዎች ጥረት ቤት ከመፍረስና ቤተሰብ ከመበተን ማዳን መቻሉን ነግሮናል። አሁን ችግሩ በመፈታቱ ቤተሰቦቹን በሰላም እያስተዳደረ ይገኛል።

“የሀገር ሽማግሌዎች ሕይወት ቀያሪ በመኾናቸው በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ እንደ ፈጣሪ ነው የሚታዩት። ችግሩ በሀገር ሽማግሌ ፈጥኖ ባይፈታ ኖሮ በየተራራው፣ በየጫካና ጥሻው ለእንግልት እዳረግ ነበር። ከሕግ አካላት ጋርም ተያዝ አልያዝም በሚል ለሌላ ወንጀል ብሎም ለሕልፈተ ሕይወት እዳረግ ነበር” ሲል የሀገር ሽማግሌዎችን ሚና ገልጿል።

ሌላኛው በሽምግልና ችግሮቻቸው ከተፈታላቸው ግለሰቦች መካከል ደግሞ አቶ ውብእግዜር መንግሥቱ አንዱ ናቸው። አቶ ውብእግዜር በአካባቢው የታወቁ አስታራቂ የሀገር ሽማግሌ ናቸው። ይኹን እንጅ አንድ ቀን ድንገት በተከፈተ ተኩስ የልጃቸውና የአንድ ግለሰብ ሕይወት በተመሳሳይ ሰዓት ያልፋል። እንደዚህ ዓይነት ማኅበራዊ ችግር ሲከሰት ቀድሞ በመድረስ የሚታወቁት የአካባቢው አለኝታ የሀገር ሽማግሌዎች ዳግም የሰው ሕይዎት እንዳይጠፋና ማኅበራዊ ሕይዎት እንዳይናጋ ደም በማድረቅ መደበኛ ሕይወት እንዲቀጥል አድርገዋል። የሚገርመው ደግሞ ችግሩን ለመፍታት ከ10 ቀናት ያልበለጠ ጊዜ ነበር የወሰደባቸው። አሁን ላይ ያ መጥፎ አጋጣሚ የፈጠረው ጥቁር ጥላ ተገፎ አብረው ይበላሉ፤ አብረው ይጠጣሉ፤ አብረው በሰላም ይኖራሉ። ልጃቸውን አጋጣሚ ያጡት አስታራቂ ሽማግሌም አኹን ላይ በተመሳሳይ ችግር ውስጥ የገቡ የአካባቢው ነዋሪዎችን በማስታረቅ ላይ ይገኛሉ።

ቄስ እንደሻው ታደሰ ደግሞ በአካባቢው በሚፈጠሩ ችግሮች ቀድመው በመድረስ የሚታወቁ የሀገር ሽማግሌ ናቸው። ቄስ እንደሻው ከእምነት አባትነት ባለፈ በሀገር ሽማግሌነት በአካባቢው የሚከሰተውን ማንኛውም የማኅበረሰብ ችግር በዕለቱ በሽምግልና ባሕል እንዲፈታ ያቀራርባሉ። ቄስ እንደሻው እንዳሉት እንደ ችግሮች ኹኔታ ባለጉዳዮችን በማቀራረብ የሽማግሌ ዳኛ ዋስ እንዲጠሩ ይደረጋል። በተለይም ደግሞ የደም እርቅ ከኾነ በሃይማኖታዊ ሥርዓት በማቀራረብ እርቅ እንደሚፈጸም ነግረውናል። በእርቅ ወቅትም የሚበላና የሚጠጣ ቀርቦ በመመገብ ጊዜው የአብሮነት እንዲኾን በምረቃ ይፈጸማል። የሽምግልና ሥርዓቱ በተለይም ደም የተቃቡ ግለሰቦችን በማስታረቅ በሰላም እንዲኖሩ መደረጉን ነው የገለጹት። ይህ የሽምግልና ሥርዓት የተደራጀ እንዲሆን ድጋፍ ቢደረግለት ደግሞ ለሀገር ሰላምና ደኅንነት መረጋገጥ ሚናው የበለጠ እንደሚጎላ አንስተዋል።

ሼህ የሱፍ ሙጨም በአካባቢው የተጋጩ ነዋሪዎችን ሲያሸማግሉ ነበር ያገኘናቸው። ሼህ የሱፍ እንዳሉት በአካባቢው የሚፈጠሩ ችግሮች ሳይባባሱ በሽምግልና ሥርዓት ቀድሞ የመፍታት ባሕሉ የጎላ ነው። በሽምግልናውም በበዳይና ተበዳይ የሚነሱ ጉዳዮች በሽማግሌዎች ተመርምሮ እርቅ ይፈጸማል። በተሸማጋዮች እርቁ እንዳይፈርስ የገንዘብ መቀጮ በውል እንዲሰፍር የማድረግ ልማድ እንዳላቸው ነግረውናል።

በአካባቢው የሽምግልና ሥርዓት
በዳይ እንደ ጥፋቱ መጠን ካሳ እንዲከፍል ይደረጋል። በመጨረሻም መሳሪያ እየዘለሉና እንደየ ሃይማኖታቸው ቃለ መሃላ እንዲፈጽሙ በማድረግ እርቅ ይፈጸማል። እርቅ በሚፈጸምበት ጊዜ እርቁን ለማጽናት ከመካከላቸው አንዱ እርቅ ያፈረሰ እንደኾነ የሚከፈል የገንዘብ መጠን ይቀመጣል።

የሕግ ታራሚዎች በይቅርታ ለመፈታት በመንግሥት የሚቀመጠውን የእርቅ ቅድመ ኹኔታ ለማሟላት የሀገር ሽማግሌዎች ሚናም የጎላ ነው። ፍርደኞች በይቅርታ እንዲፈቱ በቀበሌና በሀገር ሽማግሌዎች የተረጋገጠ ደብዳቤ ለማረሚያ ቤት በማስገባት በዳይና ተበዳይ እርቅ እንዲፈጽሙ እያደረጉ እንደሚገኙ ነው ያነሱት።

ይሕ ኹሉ ሲደረግ በአካባቢው ባሕል መሠረት ተሸማጋዮች ከሚያቀርቡት የመጠጥና ምግብ ባለፈ በመንግሥት ደመወዝ እየተከፈላቸው አይደለም። የግል ሥራቸውን በመተው ለአካባቢው ሰላም እና ለሕዝብ አብሮነት ተብሎ የሚፈጸም አባታዊ ግዴታ እንጂ።

በዚህ ኹኔታ የተፈጸመን እርቀ ሰላም አፍርሶ ዳግም ወንጀል የፈጸመ አካል እንደሌለ የሀገር ሽማግሌዎቹ ነግረውናል።

የኪንፋንዝ በገላ ወረዳ ባሕል ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አደራጀው ግዛት የወረዳውን የሽምግልና ሥርዓት በመደገፍ ለአካባቢው ሰላም መስፈን አቅም እንዲኾኑ ለማድረግ የተሠራው ሥራ ዝቅተኛ መኾኑን ገልጸዋል።

በአካባቢው የሚከሰቱ ግጭቶችን ለመፍታት እንደ ትልቅ አቅም እያገለገለ መኾኑን ያነሱት ኀላፊው በቀጣይ የሀገር የሽምግልና ሥርዓቱን በመደገፍ የአካባቢ የሚከሰቱ ችግሮች መፍቻ ለማድረግ በእቅድ ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱን ነግረውናል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሰራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼
ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/