ባሕር ዳር ፡ ግንቦት 09/2015 ዓ.ም (አሚኮ) “ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ሕዝባችንን እናሻግራለን” በሚል መሪ ሃሳብ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ባዘጋጀው ኮንፈረንስ ከ1 ሺህ 400 በላይ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ይሳተፋሉ ተብሏል፡፡
ኮንፈረንሱ ከግንቦት 10/2015 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚካሄድ የአማራ ክልል ብልጽግና ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኅላፊ ዶክተር ጋሻው አወቀ ገልጸዋል፡፡
የኮንፈረንሱ ዓላማ ወቅታዊ ፈተናዎችን እና ችግሮችን በመገምገም ጠንካራ ፓርቲ እና መንግሥት ለመመስረት የሚያስችል ጽናት እና የጋራ መግባባት መፍጠር ነው ያሉት ዶክተር ጋሻው የውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ትግል እና መተማመን ከኮንፈረንሱ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ብልጽግና እንደ ማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ በውስብስብ ችግሮች ውስጥ አልፎ የመጣ ነው፤ አሁናዊ ፈተናዎችን በሚገባ ገምግሞ እና አርሞ ለላቀ ተልዕኮ ራሱን ያዘጋጃል ብለዋል፡፡
ኮንፈረንሱ በስኬት እንዲጠናቀቅ በቂ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተደርገዋል ያሉት ዶክተር ጋሻው ከኮንፈረንሱ ኅይል የሚያሰባስብ ሠላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ የሃሳብ ትግል ይካሄድበታል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ኮንፈረንሱ የክልሉን ወቅታዊ ችግሮች እና የሕዝብን ጥያቄ መሠረት ያደረገ በመሆኑ የሚጠበቁ ግቦች ይኖራሉም ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!