የከተራ እና የጥምቀት በዓላት ሃይማኖታዊ ትውፊታቸውን ጠብቀው በሰላም እንዲከበሩ ሕዝበ ክርስቲያኑ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ጥሪ አቀረበች።

0
109

ጥር 09/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የጥምቀት በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ በፈለገ ዮርዳኖስ በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ፣ በዮርዳኖስ ባሕር የተጠመቀበትን ዕለት የሚያስታውስ ታላቅ በዓል በመሆኑም በሃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ስፍራ ይሰጠዋል።

በኢትዮጵያም በድምቀት የሚከበር ሲሆን፤ አከባበሩ ዓለም አቀፋዊ ትኩረትን የሚስብ ጭምር በመሆኑ በየዓመቱ በርካታ ቱሪስቶች ወደ ሀገር ቤት ይጎርፋሉ።

የዘንድሮውን የጥምቀት በዓል እንደ ወትሮው ኹሉ ሃይማኖታዊ ትውፊቱን ጠብቆ በደመቀ ሁኔታ ለማክበር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዝግጅት ማድረጓን በቤተ ክርስቲያኗ የብፁዕ ወ ቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤትና የውጭ ጉዳይ የበላይ ኃላፊ ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ ገልጸዋል።

በርካታ ዳያስፖራዎች ወደ ሀገር ቤት ከመምጣታቸው ጋር ተያይዞ በዓሉን ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ደማቅ እንደሚያደርገውም ገልጸዋል፡፡

ይህ ታላቅ ሃይማኖታዊ በዓል ከሕዝቡ ባህል ጋር ጥብቅ ትስስር ያለው በመሆኑም ከሃይማኖታዊ በዓልነቱ ባሻገር ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውም የጎላ መሆኑንም ነው ያነሱት።

ኢትዮጵያዊያን በዓሉን በፍቅር፣ በአንድነት እና በሕብረት የሚያከብሩት በመሆኑም በሕዝቦች መካከል ማኅበራዊ ትስስርን በማጠናከር ረገድ ትልቅ ሚና እንዳለውም ጠቅሰዋል።

የዓለም አቀፍ ቅርስ ጭምር የኾነውን ይህ በዓል ሕዝበ ክርስቲያኑ ፍጹም ሰላማዊ በኾነ እና በተረጋጋ ሁኔታ ማክበር እንደሚጠበቅበትም ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በተለይ ወጣቶች ሰላምን በማስጠበቅ፣ ሥነ-ሥርዓት በማስያዝና በማስተባበር ከዚህ ቀደም የሚያሳዩትን በጎ ተግባር አሁንም መቀጠል እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ጥንት አባቶች በዓሉ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱንና ትውፊቱን ሳይለቅ ጠብቀው ማቆየታቸውን ጠቅሰው፤የአሁኑ ትውልድም በዓሉ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ እንዲከበር እና ለትውልዱ እንዲተላለፍ የማድረግ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የጥምቀት ክብረ በዓል በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባሕላዊ ቅርስነት በ2012 ዓ.ም መመዝገቡ ይታወሳል።

#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ቲክቶክ tiktok.com @amharamediacorporation

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በዋግኽምራና በወሎ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ። https://ameco.bankofabyssinia.com/