የከተማዋን የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦትን ለማሻሻያ በ16 ሚሊየን ብር የተገነባ የፀሃይ ሃይል ማመንጫ አገልግሎት ጀምሯል።

0
65

ባሕር ዳር:ጥር 16/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የላሊበላ ከተማ የንፁህ መጠጥ ውሃን የምታገኘው ከከተማዋ በ23 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው ሹምሸሃ አካባቢ በመብራት ተስቦ ነው።

በመብራት መቆራረጥ ምክንያት ከ80 ሽህ በላይ ለሆነው ለከተማዋ ማህበረሰብ በቂ የንፁህ መጠጥ ውሃን ለማድረስ ሲቸገር መቆየቱን የከተማው ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ሲገልፅ ቆይቷል።

ተቋሙ ከዚህ ቀደም በጀኔኔተር ውሃ ለማህበረሰቡ እያደረሰ የቆየ ሲሆን ከ21.2 ሚሊዮን ብር በላይ በክልሉ መንግስትና በተለያዩ ረጅ ድርጅቶች ድጋፍ እንደተደረገለት አስታውቋል።

የከተማዋን የንፁህ መጠጥ ውሃ ለማዘመን የሚያስችል በፀሃይ ሃይል ውሃን የማመንጨትና የመግፋት ፕሮጀክት በዓለማቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር የገንዘብ ድጋፍና በክልሉ የውኃ ቢሮ አስተባባሪነት ተግባራዊ እየተደረገ ነው።

በ16 ሚሊየን ብር ወጭ የመጀመሪያው ውሃን በታዳሽ ሃይል በፀሃይ ብርሃን የመግፉት ስራም ተጠናቆ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።

የከተማው ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ሃላፊ አቶ መለሰ አየለ በመጀመሪያው የታዳሽ ሃይል ፕሮጀክት የ4 ጉድጓዶች ውሃን በፀሐይ ኃይል የመግፋት ስራ ተጠናቆ በቀን 200 ሺህ ሊትር ውሃ ማመንጨት ተችሏል። ለዚህም ደግም 204 የሶላር ፓኔሎች የተዘረጉ ሲሆን 75 ኪሎ ዋት ሃይል የማመንጨት አቅም እንዳላቸው ተናግረዋል።

በምረቃው ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ውሃና ኢነርጅ ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር ማማሩ አያሌው በነበረው ጦርነት የውሃ መሰረተ ልማቶች የወደሙ መሆኑንና ይሄን መልሶ ለመገንባት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የንፁህ መጠጥ ውሃ ግንባታን አጋር ድርጅቶችን በማስተባበር በተሻለ መልኩ እንዲገነባ ለማድረግ እየተሰራ ነው ያሉት ሃላፊው የከተማዋን የንፁህ መጠጥ ውሃ በበቂ መልኩ ለማቅረብና የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ለማገዝ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በታዳሻ ሃይል እየተሰራ ያለው ስራ በቀጣይ ሶስት ክፍሎች ያሉት ሲሆን 55 ሚሊየን ብር ወጭ የሚደረግበት ስራ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የውሃ አገልግሎቱንም በተገቢው መልኩ ማሳደግ ይገባልም ተብሏል። ቢሮው በቀጣይ የከተማዋን የንፁህ መጠጥ ውሃ ለማሻሻል ይሰራልም ብለዋል ሃላፊው።

የላሊበላ ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት በጦርነቱ ከ21 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት የወደመበት መሆኑም ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!