“የከተማና መሠረተ ልማት ባለፉት አራት ዓመታት በገጠሙት ፈተናዎች ዘርፉ ለጉዳት ተጋልጧል” የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር

24
ነጭመደበኛ
ነጭመደበኛ
አዲስ አበባ: መጋቢት 08/2015 ዓ.ም (አሚኮ)የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የመሠረተ ልማት ዘርፍ ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ምክክር እየተደረገ ነው።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ከመሠረተ ልማት ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ጋር ነው ምክክር እያደረገ ያለው፡፡ የምክክሩ ዓላማ በመሠረተ ልማት ዘርፉ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት መፍትሔ ለማስቀመጥ ነው።
በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አዳራሽ በተዘጋጀው የምክክር መድረክ የተገኙት የመሠረተ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወንድሙ ሴታ (ኢ.ር) ባለፉት 20 ዓመታት ዘርፉ ዕድገት እያስመዘገበ ቢሆንም ከአራት ዓመታት ወዲህ በገጠሙት ፈተናዎች ዘርፉ ለጉዳት ተጋልጧል ብለዋል።
በየጊዜው የሚገጥሙ ችግሮች እንዲፈቱ ከዘርፉ ተዋናዮች በተለይም ከተቋራጮች ማኅበር ጋር ተቀራርቦ ለመሥራት የተደረገው ጥረት ምስጋና የሚቸረው ነው ብለዋል።
በመድረኩ የሚነሱ ችግሮችና የመፍትሔ ሀሳቦችን ወስዶ በፖሊሲና ስትራቴጂ ለማካተት እንደሚሠራም ሚኒስትር ዴኤታው አስገንዝበዋል።
የተለያዩ ደንቦችና ማሻሻያ ሰነዶች እያዘጋጁ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ለውይይት እንዲቀርቡና የሚሻሻለው ተሻሽሎ የዘርፉን ችግር ለመቅረፍ ይሠራል ብለዋል።
በመድረኩ የውይይት መነሻ ጹሑፍ ያቀረቡት የኢትዮጵያ ተቋራጮች ማኅበር ሰብሳቢ ግርማ ኃ/ማርያም (ኢ.ር) የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን የሥራ ኀላፊዎች፣ ባለሙያዎችና የማኅበራቸው አባላት እያደረጉት ላለው አዎንታዊ ተሳትፎ አመስግነዋል፡፡
የሚገጥሙና አላሠራ ያሉ የሕግና የፖሊሲ ጉዳዮች እንዲሻሻሉ፣ የጨረታ ፣የዋስትና ፣የገንዘብ አቅም ፣ የሀገር በቀል ተቋራጮች ተጠቃሚነት፣ የማሽነሪ ፣ የተቋራጮች ደረጃ ፣የኮንስትራክሽን ኢንደስትሪ ደኅንነትና ጤና፣ የብቃት ማረጋገጫ፣ እድሳት፣የፕሮጀክት አስተዳደር ጉዳዮች እና ሌሎች በርካታ የዘርፉ ችግሮች የሚፈቱበትን መንገድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በትኩረት እንዲሠራ ጠይቀዋል። የመፍትሔ ሀሳቦችንም አቅርበው በጋራ ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ነው የገለጹት።
ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግሥቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!