የእግር ኳስ ውድድሮች በተመረጡ ሜዳዎች እንዲካሄዱ የኮሮናቫይረስ መከላከል ፕሮቶኮል መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ፡፡

0
119

ባሕር ዳር፡ መስከረም 09/2013ዓ.ም (አብመድ) የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ማኅበር ታገኝ የነበረውን 300 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር አሳጥቷል፡፡

በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ የእግር ኳስ ውድድሮችን ማቋረጥ አንዱ የቅድመ መከላከል እርምጃ ነበር፡፡ “በእግር ኳስ ዙሪያ ያሉ ባለሙያዎች፣ አሰልጣኞች፣ ተጫዋቾች ገቢ እንዳይኖራቸው ሆኗል” ሲሉ ውድድሮቹ በመቋረጣቸው ምክንያት የመጡ ተፅዕኖዎችን የነገሩን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ባሕሩ ጥላሁን ናቸው፡፡
ሁሉም ባይባሉም የእግር ኳስ ቡድኖች ደመወዝ በአግባቡ ባለመክፈል ቅሬታ ተነስቶባቸዋል፡፡
ቡድኖቹ በጨዋታ ጊዜ ወደሜዳ ከሚገባው ተመልካች ያገኙት የነበረው ገቢ ተቋርጧል፡፡ የአውሮፓውያኑ 2020 ዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ማኅበር “ፊፋ ኮንግረስ” በሚል የሚጠራው ጉባኤ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ዝግጅት ተደርጎ የኮሮና ወረርሽኝ እንቅፋት ፈጥሮበታል፡፡ በአፍሪካ ለእግር ኳስ ዕድገትና ጉባኤው በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ አንድ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በ“ፊፋ” ተመድቧል፡፡ ከዚህ ከተመደበው ገንዘብ የኢትዮጵያ ድርሻ 33 በመቶ ወይም 300 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ነው፡፡ እናም ሀገሪቱ ይህን ገንዘብ አጥታለች፡፡

እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በ“ስፖንሰርሺፕ” ያገኝ የነበረውን ገቢም አስቀርቶበታል፡፡ ለአብነት ከዋሊያ ቢራ ይገኝ የነበረው ገንዘብ ሙሉ በሙሉ መቋረጡን አቶ ባሕሩ ተናግረዋል፡፡
“የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ባይጠፋም እንዴት የእግር ኳስ ውድድሮችን ማስቀጠል ይቻላል?” በሚል የሊግ ተወካዮች የተካፈሉበት ውይይት መደረጉን ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ በፊት በተለያዩ መጫወቻ ሜዳዎች (ስታዲየም) በመዟዟር ይደረግ የነበረው የእግር ኳስ ጨዋታ በተመረጡ የተወሰኑ ሜዳዎች እንዲካሄዱ ከጤና ሚኒስቴር፣ ማኅበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና ስፖርት ኮሚሽን ጋር በመተባበር የኮሮናቫይረስ መዘጋጀቱን አቶ ባሕሩ አስረድተዋል፡፡ ውድድሮችን ለማስጀመር የመንግሥት ይሁንታ እየተጠበቀ ነው፡፡ ቡድኖች በቀዳሚነት ማድረግ የሚያስፈልጋቸውን እንዲያከናውኑም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በቅርብ ክትትል እያካሄደ ስለመሆኑ ኃላፊው ጠቅሰዋል፡፡

ከፀጥታ ጋር በተያያዘም የሚነሱ ስፖርታዊ ጨዋነት መጓደሎችን ሙሉ በሙሉ በአንዴ ማጥፋት እንደማይቻል አቶ ባሕሩ አንስተዋል፡፡ ነገር ግን በ2012 ዓ.ም እግር ኳስ ውድድሮች በኮሮናቫይረስ መከሰት ምክንያት እስከተቋረጡበት ጊዜ ድረስ ፍፁም ስፖርታዊ ጨዋነት መታየቱ እንደማይካድ ኃላፊው አመላክተዋል፡፡

“ስፖርት ለሰላም” በሚል የተለያዩ መርሀ ግብሮችና ምክክሮች ከደጋፊዎች፣ ከቡድን አስጨፋሪዎችና መሪዎች ጋር በመካሄዳቸው የመጣ ለውጥ እንደነበር አስታውቀዋል፡፡ አንዱ ቡድን ደጋፊ ከሌላኛው ጋር እንዲቀራረቡ በማድረግ እግር ኳስ ለአንድነትና ለፍቅር መሆኑን በማስገንዘብ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ወደከፍታ የሚወስድ ሥራ ማከናወን እንደሚሹም አንስተዋል፡፡ ወደፊትም ብዙኃን መገናኛዎችን በመጠቀም፣ ውይይቶችን በማዘጋጀትና ሙያተኞች ግምገማና ክትትል እንዲያደርጉ በማድረግ የተሻለ ስፖርታዊ ጨዋነት ላሳዩ እንዲበረታቱ በማድረግ በአንድ ጀምበር ለውጥ ባይመጣም ቀስ በቀስ መሻሻሎች እንዲስተዋሉ ይሠራበታል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here