የእኛ ሰው በሞሮኮ!

0
186

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ከወራት በፊት ባሕር ዳር ባዘጋጀችው 10ኛው ጣና ፎረም ጉባዔ ላይ የተገኙት እውቁ ሞሮኳዊው የፖለቲካል ሳይንስ ፕሮፌሰር ላኢድ ዛግላሚ እንዲህ አሉ “አፍሪካ እንደ አህጉር ራሷን የቻለች ነጻ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ አህጉር ኾና እንድትወጣ ከተፈለገ ለዘመናት የጸናውን የባርነት አስተሳሰብ አሽቀንጥሮ የሚጥል ሁሉን አቀፍ አዲስ አብዮት ያስፈልጋታል”፡፡

ከፕሮፌሰሩ ቁጭት የተሞላበት ንግግር የወራት ቆይታ በኋላ የአትላስ አናብስቱ በኳታሩ የዓለም ሀገራት የእግር ኳስ ድግስ ላይ አዲስ ታሪክ እና አዲስ አብዮት አስመዘገቡ፡፡ አፍሪካዊቷ ሀገር ሞሮኮ በዓለም የእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ግማሽ ፍጻሜውን የተቀላቀለች አፍሪካዊት ሀገር ኾነች፡፡ አውሮፓዊያን የእግር ኳስ ጠበብት ሀገራት በኳታሩ የዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ውድድሮች ተሳትፎ በሞሮኮ ፊት ተፈሪነታቸውን እና አሸናፊነታቸውን ሲነጠቁ ተመለከትን፡፡

ከዘጠኝ አስርት ዓመታት በላይ በዘለቀው የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ታሪክ ውስጥ ሞሮኮ ለአህጉሪቷ አዲስ የእግር ኳስ ታሪክ ጽፋለች፡፡ በ1934ቱ የዓለም ዋንጫ ውድድር ግብጽ አንድ ብላ አህጉሪቷን ከወከለችበት ጊዜ ጀምሮ ከ88 ዓመታት ትዕግስት እና ጽናት በኋላ ሞሮኮ አፍሪካን በዓለም ዋንጫ ለግማሽ ፍጻሜ እንድትወከል ምክንያት ኾነች፡፡

ምዕራባዊያኑን የእግር ኳስ ባለታሪክ ሀገራት በብርቱ ትግል ድል እያደረገች ለግማሽ ፍጻሜ ፍልሚያ የደረሰችው ሞሮኮ አፍሪካዊ ማንነት ያለው እግር ኳስ እንደገነባች ዛሬዋን ሳይሆን ትናንትናዋን ዋቢ አድርገው የሚሞግቱት በዝተዋል፡፡

በአፍሪካ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ አያሌ አህጉራዊ አበርክቶ ካላቸው የዘርፉ ታላላቅ ሰዎች መካከል ግንባር ቀደሙ ኢትዮጵያዊው የስፖርት ሰው ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ለ58 ዓመታት በስፖርት ዓለም ውስጥ ጉልህ ሀገራዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተሳትፎ የነበራቸው ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ ከተጫዋችነት እስከ ስፖርት አመራርነት የዘለቀው ጉዟቸው በስኬቶች የታጀበ ነበር፡፡

ገና በስምንት ዓመት እድሜያቸው ወደ ስፖርቱ ዓለም የተቀላቀሉት እኝህ ታላቅ የስፖርት ሰው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን የመሰረቱ እና ከ15 ጊዜያት በላይ ሀገራቸውን በአምበልነት መርተው የተጫዎቱ ብርቱ የስፖርት ሰው እንደነበሩ ይነገርላቸዋል፡፡ ሁለገቡ የስፖርት ሰው ከእግር ኳስ በዘለለ በአትሌቲክስ፣ ቦክስ እና ብስክሌት ስፖርታዊ ውድድሮችም አበርክቷቸው ዘርፈ ብዙም ነበር፡፡

ከሀገር ተሻግሮ ለአህጉራዊ የስፖርት እድገት ጉልህ የአመራር ተሳትፎ የነበራቸው ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ በዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ዘንድም አንቱታን ያተረፉ ባለውለታ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል፡፡ ሀገራቸውን ብቻ ሳይሆን አህጉራቸውንም በመወከል አፍሪካ በዓለም የስፖርቱ ቤተሰብ ዘንድ ውክልና ይኖራት ዘንድ ፈር ቀዳጅ ኾነው አልፈዋል፡፡

የአፍሪካ ብሔራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴ መስራችና አባል፣ የአፍሪካ የስፖርት ኮንፌዴሬሽኖች ኅብረት መስራችና ፕሬዝዳንት፣ የአፍሪካ የብሔራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር መስራችና የክብር ፕሬዝዳንት፣ የአፍሪካ የስፖርት ሚኒስትሮች ካውንስል ቋሚ የሥራ አስፈጻሚ፣ የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ፕሬዝዳንት አበርክቷቸው ጉልህ እንደነበር ታሪክ አይዘነጋውም፡፡

ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ ሀገራቸውን እና አህጉራቸውን ወክለው በስፖርቱ ዓለም ትውልድ የማይዘነጋው አሻራ አስቀምጠው ቢያልፍም ሀገራቸው የአበርክቷቸውን ያክል ዘክራቸዋለች ተብሎ ግን አይታሰብም፡፡ በአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ ያሉ ስታዲየሞች ያልዘከሯቸው የስፖርቱ ባለአደራ ሰው ሞሮኮ ክብራቸውንም ስማቸውንም በሚመጥን ልክ የስታዲየም ስያሜ ሰጥታ አፍሪካን በትዝብት ዓለምን በግርምት ደግመው እና ደጋግመው እንዲያስቡ አድርጋለች፡፡
የእኛ ሰው በእኛ ሀገር የአበርክቷቸውን ያክል ባይዘከሩም፤ የእኛ ሰው በሞሮኮ ግን በልፋታቸው ልክ ተዘክረዋል፡፡ ሞሮኮም ከ88 ዓመታት የዓለም ዋንጫ አህጉራዊ መቆዘም በኋላ አዲስ ታሪክ እና አዲስ ገድል በአትላስ አናብስቶቹ አስመዝግባለች፡፡ እግር ኳስ በሰጡት ክብር እና ትጋት ልክ ውጤት እና ድል ይሰጣልና ሞሮኮ የዘራችውን አጭዳለች፡፡ ዛሬም ሌላ ቀን ነው፤ አፍሪካም በሞሮኮ ውክልና ለአዲስ ታሪክ እና አዲስ ገድል ዛሬ ከአውሮፓዊቷ ሀገር ፈረንሳይ ጋር የላቀ ተጋድሎን በኳታር ታደርጋለች፡፡

መልካም እድል ለአፍሪካ እግር ኳስ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ተመኘን!

በታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!