የእንግሊዙ ዘ ቴሌግራፍ ያወጣውን የተሳሳተ መረጃ እንደገና እንዲያርም የኢትዮጵያ ወቅታዊ መረጃ ማጣሪያ ጠየቀ፡፡

0
126
ጥቅምት 10/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ለወትሮውም የኢትዮጵያ መልካም ዜና የማይመቻቸው ምዕራባውያን ብዙኃን መገናኛ አሁንም የበሬ ወለደ መረጃዎችን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማሰራጨታቸውን ቀጥለዋል፡፡ በተለይ ሽብርተኛው ትህነግ ሀገር የማፍረስ ተግባሩ እንዳይሳካ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጫፍ ጫፍ ተነስቶ ተገቢውን ቅጣት መስጠት ከጀመረ ወዲህ ከሙያዊ ሥነ ምግባር ባፈነገጠ መልኩ የተዛቡ ዘገባዎችን ሲሠሩ አስተውለናል፡፡
የሲኤን ኤን፣ የቢቢሲ፣ አልጀዚራ እና መሰል ዓለም አቀፋዊ ብዙኃን መገናኛ በነ ኢራቅ፣ የመን፣ ሶሪያ እና መሰል ሀገራት የሠሩትን ሕዝብ የመከፋፈል እና ሀገር የማፍረስ ደባ ባለ በሌለ አቅማቸው ኢትዮጵያ ላይ እየሞከሩ ነው፡፡
ሰሞኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የግብርና ምርትና ምርታማነትን በእጥፍ በማሳደግ ከተረጂነት መውጣት ግድ ይላል ብለው የገለጹትን የእንግሊዙ ዘ ቴሌግራፍ ጋዜጣ “የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ሀገሪቱ የሚገባውን የምግብ ዕርዳታ ሊያስቆሙ ነው” ብሎ የተዛባና ከእውነት የራቀ ዘገባ ሠርቷል፡፡ የኢትዮጵያ ወቅታዊ መረጃ ማጣሪያ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንደገለጸው ቴሌግራፍ ስለ ኢትዮጵያ የተሳሳተ መረጃ ለተደራሲው ማሰራጨቱን ቀጥሏል፡፡
የሽብርተኛው ትህነግ አሰቃቂ ወንጀሎች የማይታዩት ቴሌግራፍ በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን የስም ማጥፋት ዘመቻ ለማጠናከር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ንግግር በማንሻፈፍ አንባቢውን እያደናገረ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ግብርናዋን በማዘመን እና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ሰብል ራሷን ትችላለች፤ ከተረጂነትም ራሷን ታላቅቃለች የሚል አገላለጽ ያለውን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ንግግር ጋዜጣው አዛብቷል፡፡ የኢትዮጵያ ወቅታዊ መረጃ ማጣሪያ ቴሌግራፍ እውነታውን ማወቅ ለሚፈልጉ ተደራሲያኑ ትክክለኛውን መረጃ ለማድረስ የቋንቋ እገዛ የሚያስፈልገው ከሆነም ድጋፍ መጠየቅ እንደነበረበት ለጋዜጣው በጻፈው ደብዳቤ ገልጿል፡፡
ቴሌግራፍ ባወጣው መረጃ የሠራው ስህተት እውነታውን ከአውዱ ውጭ ከመግለጽ ወይም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር በተሳሳተ መንገድ ከመተርጎም ያለፈ ነው። ይህም ደንታ ቢስነት እና በአጀንዳ ላይ የተመሠረተ ዘገባን ሙሉ በሙሉ ማጣመም ነው ሲል ገልጾታል። ለሙያው ሲባል ቴሌግራፍ ይህንን ዘገባ እንደገና መገምገም እና የጋዜጠኝነት ደረጃዎችን ያሟላ እንዲሆን ማድረግ እንዳለበት ተጠይቋል፡፡
በየማነብርሃን ጌታቸው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ