የእንስሳት ግብይት ዋጋ መጨመሩን ገዥዎች ተናገሩ፡፡

0
117
የእንስሳት ግብይት ዋጋ መጨመሩን ገዥዎች ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 22/2013 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ የእንስሳት ግብይት ምልከታ አድርጓል። በምልከታዉም በዶሮ፣ በግና ከብት ላይ አንጻራዊና ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ መኖሩን አንዳንድ የኅብረተሰብ ክፍሎች አረጋግጠውልናል።
አቶ ምትኩ አፈወርቅ የሚኖሩት በባሕር ዳር ከተማ ነው። ለበዓል በግ ሲገዙ ነበር ያገኘናቸው። በገበያ የበግ አቅርቦት በብዛት ቢታይም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በአማካይ በአንድ በግ ላይ የ500 ብር ጭማሪ እንዳለ ተናግረዋል።
አቶ ንጉሤ ፍቅሬ ደግሞ የበግ ነጋዴ ናቸው። የዋጋ ጭማሪው እንደ በግ አይነቱ የሚለያይ ሆኾ በሁሉም የበግ አይነት ላይ ግን የዋጋ ጭማሪ መታየቱን ተናግረዋል። ለዋጋ መጨመሩ ምክንያት ከአርሶ አደሮች የሚገዙበት ዋጋ ጭማሪ ስላለው ነው ብለዋል። በአማካይ አንድ በግ ከ2 ሺህ 500 እስከ 8 ሺህ ብር ድረስ እንደሚሸጥ ተናግረዋል። ነጋዴውም ቢሆን በጎችን ከአርሶ አደሮች ዋጋ ጨምሮ ከገዛ በኋላ የመኖ ወጪ ስለሚኖርበት ቀንሶ ቢሸጥ ለኪሳራ ሊጋለጥ ይችላል ብለዋል።
ሌላው አሚኮ ተዘዋውሮ ከተመለከታቸው ውስጥ የከብት ገበያ አንዱ ነበር። ሻለቃ አማረ ሲሳይ ለበዓል ከብት ለመግዛት ቅኝት ሲያደርጉ ነበር ያገኘናቸው። ባለፈው ዓመት በርካታ የከብት አቅርቦት በገበያው እንደነበረ አስታውሰው ዛሬ ግን ገብያው ሙሉ ነው ማለት አይቻልም ብለዋል። “እኔ በ15 ሺህ ብር ነበር ለመግዛት ወደ ገበያ የወጣሁት ነገር ግን ለመግዛት ያሰብኩት ከብት 23 ሺህ ብር ደርሶ አግኝቼዋለሁ” ብለዋል።
አቶ እውነቱ ሞገስ የተባሉ የከብት ነጋዴ ደግሞ በከብትም ሆነ በመኖ የዋጋ ጭማሪ መኖሩን ተናግረዋል። ባለፈው ዓመት በዚሁ ወቅት 20 ሺህ ብር የነበረው ከብት አሁን 30 ሺህ ብር እየተሸጠ መሆኑንም ነግረውናል፡፡ ነጋዴው ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃጸር 50 በመቶ ዋጋ ጨምሯል ብለዋል። መካከለኛ ሰንጋ 30 ሺህ ብር ሲያወጣ የደለበ ሰንጋ ደግሞ እስከ 60 ሺህ ብር ድረስ እንደሚሸጥ ጠቁመዋል።
አቶ ዘውድነህ ዘገዬ የዶሮ ነጋዴ ናቸው። እንደ ዶሮ አይነት ዋጋ የሚለያይ መሆኑን ነግረውናል፡፡ አንድ ዶሮ ከ250 እስከ 400 ብር እየተሸጠ መሆኑንም ገልጸዋል።
ዶሮ እየገዙ ያገኘናቸው ወይዘሮ ወይንሸት ፋንታሁን፣ በዶሮ ላይ የጎላ ጭማሪ የለም ብለዋል። በ300 ብር የተሻለ ዶሮ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ብሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here