የኢኮኖሚው ዋልታ ሊኾን የሚገባው ቡና በአማራ ክልል

0
130

ነሐሴ 04/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከ4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ይታረሳል። ከ240 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ይለማል። እስካሁን ከ33 ሺህ 334 ሄክታር በላይ መሬት በቡና ተክል ተሸፍኗል። ቡና በ21 ወረዳዎች በ5 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በኩታገጠም እንደሚለማ ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወጣት አቤልነህ ወርቁ ይባላል። በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጓንጓ ወረዳ ዳንጉራ ቀበሌ ነዋሪ ነው። ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ቡና ያመርታል። ወደዚህ ዘርፍ ከመግባቱ በፊት ድንች እያመረተ ሕይወቱን ይመራ እንደነበር ገልጾልናል። ወጣት አቤልነህ በተለያዬ ጊዜ ያገኘውን ሥልጠና ኑሮውን ለውጦለታል። እያመረተ ያለው ቡና ለዓለም ገበያ ቀርቦ የተሻለ ዋጋ በማግኘቱ በዚህ ዓመት ከ40 ኩንታል በላይ ጀንፈል (ያልተፈለፈለ) ቡና ለማምረት አቅዶ እየሠራ መኾኑንም ነግሮናል።

አቤልነህ አንድ ኩንታል ጀንፈል ቡና በዓለም ገበያ ከ22 ሽህ ብር በላይ እየተሸጠ መኾኑ ለእኔ ተመራጭ ነው ብሏል። በአካባቢው ያሉት አርሶ አደሮች በዘርፉ እንዲሰማሩ እና ሕይወታቸውን እንዲለውጡም መክሯል።

አቤልነህ በውኃ እጥረት ምክንያት የሚከሰትን የምርት መቀነስን ለማስቀረት የባለሙያ ድጋፍ እንደሚያስፈልገውም ጠቅሷል።

ሌላው ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ጋር ቆይታ የነበራቸው ቆሞስ መላከ ምኅረት አያና ይባላሉ። በጓንጓ ወረዳ ስጋዲ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። ቆሞስ መላከ ምኅረት ቡና ማምረት ከጀመሩ ዓመታትን አስቆጥረዋል። ቆሞስ መላከምኅረት አያና በተለያዬ ቦታ በመዘዋወር የቀሰሙት ልምድ ለውጤት አብቅቷቸዋል።

ቆሞስ መላከ ምኅረት ልጆቻቸውንም በአግባቡ እያስተማሩ ነው። አልፎ አልፎ የቡና በሽታ ተከስቶ የምርት መቀነስ ቢያጋጥማቸውም ከባለሙያ የሚሠጠውን ምክረ ሐሳብ ተግባራዊ በማድረጋቸው ለውጥ ማምጣት እንደቻሉ ነግረውናል።

በጓንጓ ወረዳ ግብርና ጽሐፈት ቤት የአትክልትና ፍራፍሬ ቡድን መሪ ካሴ አደመ በወረዳው ከ1 ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት በቡና ተክል መሸፈኑን ነግረውናል።

አቶ ካሴ አካባቢው ለቡና ምርት የተሻለ መኾኑን ጠቁመው በ2013 ዓ.ም 102 ኩንታል ቡና ለማኅበራት መሸጡን ነግረውናል። በወረዳው ሦስት አርሶአደሮች ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ፈቃድ ወስደው እየሠሩ መኾኑን የጠቆሙት ቡድን መሪው ሌሎች አርሶአደሮች በዘርፉ እንዲሠማሩ ጥረት እየተደረገ መኾኑን ነግረውናል።

በባህላዊ መንገድ ያመርቱ የነበሩ አርሶአደሮችን ወደ ዘመናዊ አመራረት ለማስገባት በተደረገ ጥረት ከ15 ሄክታር በላይ የቡና ማሳ የምርት ጭማሪ መምጣቱን ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የአትክልት እና ፍራፍሬ መስኖ ውኃ አጠቃቀም ባለሙያ አወቀ ዘላለም በአማራ ክልል ከ33 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና እየለማ መኾኑን ተናግረዋል።

በክልሉ 20 ማኅበራት እና አንድ ዩኒየን ተቋቁመው እየሠሩ መኾኑን ጠቁመዋል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት 511 ኩንታል ቡና ለውጭ ገበያ ቀርቧል ያሉት አቶ አወቀ በቀጣይ የተሻለ ለማምረት ከተዘጋጁት 7 ነጥብ 9 ሚሊዮን ችግኞች 6 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ለአርሶ አደሮች የተሠራጩ መኾኑን ተናግረዋል።

ከክልሉ በተጨማሪ አየሁ እርሻ ልማት 972 ኩንታል ቡና ለውጭ ገበያ ማቅረቡንም ገልጸዋል።

ቡናን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ማምረት ብቻ ሳይኾን በማድረቅ ወቅት የሚከሰትን የጥራት መጓደል ለማሻሻል እየሠሩ መኾኑንም ተናግረዋል። አርሶአደሮችም ይኽን ተገንዝበው በአግባቡ በማምረት ተጠቃሚነታቸውን እንዲያሳድጉ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በየዓመቱ የሙያም ኾነ የገንዘብ ድጋፍ ይደረጋል ያሉት አቶ አወቀ አርሶ አደሮች ችግኞችን በወቅቱ በመትከል ኀላፊነታቸው እንዲወጡ አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ:- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼

ከእኛ ጋር ስለኾኑ እናመሰግናለን‼

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J

በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/