የኢንዱስትሪ ፓርኮችን መሰረተ ልማት በማሟላት ለባለ ሃብቶች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እየተሠራ ነው።

0
20

ደሴ: ግንቦት 26/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በኮምቦልቻ ከተማ የሚገኙ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለማልማትና ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ በትኩረት እየሠራ መሆኑን በአማራ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን የኮምቦልቻ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እሸቱ አሊ ገልጸዋል። ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በተከናወነው ሥራ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ቁጥር ከ3 ወደ 5 ከፍ እንዲል ተደርጓል ብለዋል። በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ውስጥ ይሠሩ የነበሩ ባለሃብቶች ቁጥርም ከ65 ወደ 155 አድጓል ነው ያሉት።
ለፓርኮች ተከልሎ እየለማ ያለው መሬት ከ360 ሄክታር በላይ መድረሱን የገለጹት አቶ እሸቱ ባለፉት ዓመታት የባለ ሃብቶችን አፈጻጸም ለማሻሻል በተደረገው ጥረት ከክልሉ መንግሥት 18 ሚሊየን ብር፣ ከኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ደግሞ 5 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ተመድቦ የመንገድና መብራት መሠረተ ልማቶችን የማስፋፋት ሥራ መከናወኑን አስታውቀዋል።
በፓርኮች የሚታየውን የኃይል መቆራረጥ ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት ከ42 ሚሊየን ብር በላይ ለትራንስፎርመርና መስመር ዝርጋታ ተከፍሎ የኃይል አቅርቦት እንዲሟላ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነም ተገልጿል።
ባለ ሃብቶች በጠየቁት የሊዝና ፕሮጀክት ፋይናንስ ብድር አቅርቦት መሰረትም 20 ባለ ሃብቶች ከሁለት ቢሊየን 586 ሚሊየን ብር በላይ ብድር እንድወስዱ ተደርጓል ብለዋል።
በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሚገኙ ፋብሪካዎች ከ1 ሺህ 400 በላይ ቋሚና ከ580 በላይ ጊዜያዊ በአጠቃላይ ከ2ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወገኖች የሥራ እድል መፍጠራቸውን የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ እሸቱ ተናግረዋል።
በከተማው የተለያዩ አካባቢዎች ለኢንቨስትመንት መሬት የወሰዱ እና በአግባቡ ባላለሙ ባለሃብቶች ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የገለጹት አቶ እሸቱ በሂደቱም 34 ባለ ሃብቶች ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል ብለዋል። ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ባለሃብቶች በ10 ቀናት ውስጥ በቀጣይ ስለሚያከናውኗቸው ተግባራት በቂ መረጃ ማቅረብ ካልቻሉ ከመንግስት የወሰዱት መሬት ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ ይደረጋል ነው ያሉት። ይህም በፍጥነት ወደ ልማት ለሚገቡ ባለ ሃብቶች እንዲተላለፍ ለማድረግም ከወዲሁ እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል።
ዘጋቢ:–አሊ ይመር
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/