ባሕር ዳር፡ ግንቦት 18/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮ-ቻይና ሁለንተናዊና ስትራቴጂካዊ የትብብር አጋርነት ተጨባጭ ውጤት ማምጣቱን የቻይና ምክትል ፕሬዝዳንት ሀን ዤንግ ገለጹ።
ምክትል ፕሬዝዳንቱ የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንን ተቀብለው አነገጋረዋል።
የኢትዮ-ቻይና ሁለንተናዊና ስትራቴጂካዊ የትብብር አጋርነት ተጨባጭ ውጤት ማምጣቱን ሀን ዤንግ ገልጸዋል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተደረገው ጉብኝት ይህንኑ ግንኙነት ለማጠናከር የተሻለ እድል ይፈጥራል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ሰላምን ለማጽናት መልሶ ማቋቋምና ዳግም ግንባታ እንዲሳካ ለምታደርገው ጥረት ቻይና አስፈላጊውን ትብብር እንደምታደርግ ተናግረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በዚሁ ወቅት ቻይና ለምታደርጋቸው ሁለንተናዊ ድጋፎች ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ባለፉት ሶስት አመታት ቻይና ከኢትዮጵያ ጎን በመሆን በዓለም አቀፍ መድረኮች ላሳየችው በመርህ ላይ የተመሰረቱ አቋሞች አድንቀዋል።
የሀገራቱን ግንኙነት የበለጠ በማጠናከር በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት እንደሚገባ መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!