“የኢትዮጵያ ፈተናዎች ምንጫቸው የውጭ ኃይሎች ጣልቃገብነት፤ የድል ምስጢሮቿ የሕዝቦቿ የውስጥ አንድነት ናቸው”

0
53

እንጅባራ: ሕዳር 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በዘመን ሽግግሮች ሁሉ ዘመን አመጣሽ ፈተና እና መከራ እጅጉን ሲፈትኗት አልፈዋል። ነገር ግን ለፈተናዎቿ ሸብረክ፤ ለመከራዎቿ በርከክ ያለችበት ወቅት በታሪክ አጋጣሚዎች ሁሉ እምብዛም አልተስተዋሉም። እንደ ፈተናዎቿ ብዛት፤ እንደ ፈተኞቿ ብርታት ቢሆን ኖሮ ግን ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር በዓለም ካርታ ውስጥ ፈጽሞ በጠፋች ነበር።

የቀንዱ ክስተት የሆነችው ኢትዮጰያ ቀንዳም ጣልቃገቦች እና አሳልፈው የሚሰጧት የውስጥ አኩራፊዎች እየተናበቡ መንገዷን ጠመዝማዛ እና ውጣ ውረዷን የበዛበት ሲያደርጓት ቆይተዋል። የቴዎድሮስ ታላቅ ሀገር የመገንባት ራዕይ የጨለመው፤ የምኒልክ ሌጋሲ በተከታዮቹ መቀጠል የተሳነው በትባበሩ እና በተቀነባበሩ የውስጥ እና የውጭ ሴራዎች ነበር። እንዲያም ሆኖ ግን ኢትዮጵያዊያን በብሂላቸው በፈተና ብዛት እና በመከራ ብርታት የማይታጠፉ ልጆች ስላሏት እንደ ሀገር መቀጠል ችላለች።

ኢትዮጵያ የመጣችበት መንገድ አድካሚ፤ የእድገት ሂደቷም አዝጋሚ ቢሆንም ማንነቱን ያልጣለ፤ ነጻነቱን ያላስደፈረ ትውልድ በየጊዜው አልታጣም። ከአድዋ እስከ ካራ ማራ፤ ከሰገሌ እስከ ዶጋሌ የወጓትን መክታ፤ ያኮረፏትን አግባብታ ነጻነቷን ጠብቃ ዘልቃለች። በምኒልክ ዘመን ጉልቶ እንደተጀመረ የሚነገርለት የኢትዮጵያ ኦፌሲላዊ የውጭ ግንኙነትም በጦርነት ክንደ ብርቱ፤ በዲፕሎማሲ አንደበተ ርቱዕ በሆኑ ልጆቿ ደግመው ደጋግመው አኩሪ የአሸናፊነት ታሪክን እያጎናጸፏት አልፈዋል።

አሁናዊቷ ኢትዮጵያም የቀደመውን አይነት ፈተና፤ ያለፈ ዘመኗን የሚያስታውስ መከራ ሲፈትናት ታይቷል።

ላለፉት ሁለት እና ሦስት ዓመታት በጦርነት ስትፈተን የቆየችው ኢትዮጵያ የሰላም አየር የምታገኝበት የሚመስል የሰላም ጭላንጭሎች ታይተዋል። ሀገሪቱ ለዘመናት በጸናው “አፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ ይሻሉ” አቋሟ የውስጥ ግጭቶቿን ሰላማዊ በሆነ መንገድ የሚቋጩ የሰላም በሮች በአፍሪካ ሕብረት በኩል ተከፍተዋል። ኢትዮጵያም ምንጊዜም ቢሆን ለሰላም የማይታጠፉ እጆቿን የሰላም በሮቹን በቅንነት በመክፈት በድጋሚ አሳይታለች።

ትናንት ከአልጀርስ እስከ በራስልስ ለሰላም አማራጮች ቀናዒ የነበረችው ኢትዮጵያ ዛሬም ከፕሪቶሪያ እስከ ኬኒያ ለሰላም እጆቿ እንደማይታጠፉ ልጆቿም እንደማይሰንፉ በድጋሚ አረጋግጣለች። ኢትዮጵያ በሉዓላዊነቷ ድርድር፤ በብሔራዊ ጥቅሞቿ ክርክር ባትፈልግም ጦርነት እና የኃይል አማራጭ ብቸኛ መንገዷ እንዳልሆኑም አስመስክራለች።

ላለፉት ሁለት እና ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያ የዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት የተለያየ ሚና ያላቸው በርካታ ተሳታፊዎች ነበሩበት ያሉን በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል የውጭ ጉዳይ እና ዲፕሎማሲ መምህር የሆኑት አሕመድ ዑስማን ናቸው፡፡ የእርስ በእርስ ጦርነቱ ከዘማቾች ጀርባ የተሰለፉ አዝማቾችም ነበሩበት ያሉት መምህሩ ፍላጎታቸውም ዘመንን የተሻገረ እና ኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረ ጣልቃገብነት ነበር ይላሉ፡፡ ጣልቃገብነቱ የመነጨበት የራሱ የሆኑ ታሪካዊ እና ተደጋጋሚ ምክንያቶች እንዳሉት በማመላከት፡፡

ኢትዮጵያ ጦርነቱ ከመጀመሩ ጀምሮ በርካታ የሰላም አማራጮችን እና ፍላጎቶችን መደበኛ በሆነ እና ኢ-መደበኛ በሆነ መንገድ አሳይታለች ያሉት መምህሩ መቀበል የሚፈልግ ኃይል ባለመኖሩ ጦርነቱን አይቀሬ አድርጎት ነበርም ነው ያሉት፡፡ ጦርነቱ የበዛ ውድመት እና ውድ የሰው ሕይዎት ከማሳጣቱም በላይ ደካማ መንግሥት እና ሀገር የማየት ፍላጎት የነበራቸውን የውጭ ኃይሎች ሙሉ አቅማቸውን እንዲጠቀሙ አድርጓቸዋል ብለዋል፡፡ በሂደቱም ለሁለቱም ወገኖች የማይጠቅም አስከፊ ዋጋ ተከፍሏል ብለዋል፡፡

ዘግይቶም ቢሆን በአፍሪካ ሕብረት በኩል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት መፈጸም እና ማስፈጸም ጥቅሙ ለኢትዮጵያ ነው ያሉት መምህር አህመድ “የኢትዮጵያ ፈተናዎች ምንጫቸው የውጭ ኃይሎች ጣልቃገብነት፤ የድል ምስጢሮቿ የሕዝቦቿ የውስጥ አንድነት ናቸው” ብለዋል፡፡ ለሰላም ስምምነቱ ተፈጻሚነትም ዜጎች የጀመሩትን ፐብሊክ ዲፕሎማሲ አጠናክረው በማስቀጠል ጣለቃገቦቹን ማርገብ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J