የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ለተፈናቀሉ ወገኖች ማቋቋሚያ 4 ሚሊዬን ብር ድጋፍ አደረገች፡፡

0
134

ባሕርዳር፡ ታኅሣሥ 20/2014 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በአማራ እና በአፋር ክልል ወረራ በመፈጸም ንጹሃንን ገድሏል፤ አፈናቅሏል፤ ንብረት ዘርፏል፤ አውድሟል፡፡ ይህንን ውድመት መልሶ ለመገንባት ሀገራዊ ጥሪ ተላልፏል፡፡ የባሕር ዳር ሀገረ ስብከትም ጥሪውን ተቀብሎ በሥሩ የሚገኙ ገዳማት እና አብያተክርስቲያናትን በማስተባበር ለተፈናቀሉ ወገኖች 4 ሚሊዬን ብር የሚገመት የዓይነት ድጋፍ አድርጓል፡፡
ድጋፉን ያስረከቡት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል አቡነ አብርሃም በመጽሐፈ እያሱ ምዕራፍ 10 ከቁጥር 6 ”ባሪያዎችህን ለመርዳት እጅህን አትመልስ” ተብሎ ተጽፏል፤ ይህንን መሠረት አድርጋ ቅድስት ቤተክርስቲያን መከራውን በመመልከት ድጋፍ ስታደርግ መቆየቷን ገልጸዋል፡፡ አሁንም ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ሀገራዊ ርብርብ የድርሻዋን ለመወጣት የቻለችውን አድርጋለች፤ ወደፊትም አጠናክራ ትቀጥላለች ነው ያሉት፡፡

ድጋፉ በባሕር ዳር ሀገረ ሥብከት ሥር ከሚገኙ ገዳማት እና አብያተክርስቲያናት ሠራተኞች የተውጣጣ ነው ብለዋል፡፡
ድጋፉን የተረከቡት የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳህሉ (ዶክተር) ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ዶክተር ድረስ ድጋፉ በጦርነቱ ለተጎዱ አካባቢዎች ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ ቀደም ብላ ከመተከል ዞን ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ ስታደርግ መቆየቷን አስታውሰዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ!
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ!
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ!
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ!