ባሕር ዳር፡ ግንቦት 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ 11ኛው ኮተን፣ ቴክስታይል እና አልባሳት ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው፡፡ በኮንፈረንሱ ላይ የተገኙት በደቡብ አፍሪካ ሳይንስ እና ኢኖቬሽን ዩኒቨርሲቲ መምህር እና ተማራመሪ ፕሮፌሰር ማመሞ ሙጨ ኢትዮጵያ እውቀትም የጥሬ እቃ ባለቤትም ናት ፤ ነገር ግን ቴክኖሎጂ ባለመጠቀማችን ምክንያት የራሳችንን ልብስ በአግባቡ ሳንጠቀም የሌሎችን በውድ ዋጋ ገዝተን መልበስ ልናቆም ይገባል ብለዋል፡፡ የሥራ ባሕላችንን በመቀየር ለምርምር እና ለጥበባ ፈጠራ ትኩረት በማድረግ እና የሌሎች ሀገሮችን ተሞክሮ በመውሰድ የሀገር ውስጥ አልባሳትን የተሻለ እሴት ጨምሮ ለዓለም አቀፍ ገበያ ማቅረብ ይገባል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቴክስታይል እና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ታምራት ተስፋዬ (ዶ.ር) ኮንፈረንሱ የ”ኢትዮጵያ ታምርት” ፍላጎትን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሚረዱ ግብዓቶች የሚገኙበት ነው ብለዋል። በተለይ ሀገር ውስጥ ያሉ ካምፓኒዎች ምርትን በማቅረብ ሚናቸውን እንዲወጡ ለማድረግ የተሻለ መንገድ ይፈጥራል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ቴክስታይል እና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩቱ የባሕር ዳር ከተማን የፋሽን ከተማ ለማድረግ እየሠራ መኾኑንም ዶክተር ታምራት ገልጸዋል። የባሕር ዳር ቴክኖሎጅ ኢንስትቲዩት ወደ ውጭ የሚወጡ ምርቶች የሚጨምሩበትን እንዲሁም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገነቡ ምርቶች የሚቀንሱበትን አሠራር እውን ለማድረግ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡
የዱናሚስ ማኅበራዊ ሥራ ፈጣሪዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ የተማረ አወቀ፤ የኢትዮጵያ የፋሽን ኢንዱስትሪ ከዓለም ሀገራት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ቢኾንም ዓለም ከደረሰበት ደረጃ ላይ ለመድረስ መሥራት ይጠበቃል ብለዋል፡፡ እያደጉ ያሉ ሀገሮች ሁሉንም ነገር በሀገራቸው አያመርቱም፡፡ ምርት ከሌላ በማስመጣት እና እሴት በመጨመር ሀገራቸውን ያስተዋውቃሉ እንጅ ብለዋል፡፡ የሀገራቱን ተሞክሮ በመውሰድ የተሻለ ምርት ማምረት አለብን ብለዋል፡፡ በዘርፉ የተሠማሩ አካላትን በአጫጭር ሥልጠናዎች በማብቃት ሀገራዊ ጥቅም እንዲሠጡ ማስቻል ይገባል ብለዋል አቶ የተማረ አወቀ፡፡ የፋሽን ኢንዱስትሪው እንዲያድግ እና ለሀገራዊ ኢኮኖሚው ድርሻውን እንዲወጣ የአመላካከት ለውጥ መምጣት አለበትም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!