የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሩዋንዳ አቻው ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ ሊያደርግ ነው።

151
ባሕርዳር: መጋቢት 05/2015 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሩዋንዳ አቻው ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ የፊታችን እሁድ ያደርጋል።
ብሔራዊ ቡድኑ ከጊኒ ለሚያደርገው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ነገ ዝገጅቱን ማድረግ እንደሚጀምር ተገልጿል።
የኢትዮጵያ እና ሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ የፊታችን እሁድ መጋቢት 10 ቀን 2015 ዓ.ም በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም እንደሚደረግ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
የአቋም መለኪያ ጨዋታው ዋልያዎቹ ከጊኒ ጋር ለሚያደርጉት የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ዝግጅት እንዲረዳቸው መዘጋጀቱን ገልጿል።
በኮትዲቭዋር አስተናጋጅነት እ.አ.አ በ2023 በሚካሄደው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ኢትዮጵያ ከጊኒ ጋር በሞሮኮ ራባት መጋቢት 15 እና 18 ቀን 2015 ዓ.ም ጨዋታዋን ታደርጋለች።
የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ ማድረጋቸው የሚታወስ ሲኾን ተጫዋቾቹ ነገ ዝግጅታቸውን እንደሚጀምሩ ፌዴሬሽኑ ገልጿል።
በተያያዘ ዜና ለጊኒው ጨዋታ ጥሪ ከተደረገላቸው ተጫዋቾች አንዱ የነበረው የማሜሎዲ ሳንዳውንስ አጥቂ አቡበከር ናስር ከጉዳቱ ሙሉ ለሙሉ ማገገም ባለመቻሉ ከዋልያዎቹ ስብስብ ውጪ መሆኑ ተረጋግጧል።
በምትኩም የኢትዮጵያ መድን አጥቂ የኾነውና በቻን ውድድር ላይ የብሔራዊ ቡድን አባል የነበረው ኪቲካ ጀማ ጥሪ እንደተደረገለት ፌዴሬሽኑ አመልክቷል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ አራት ከግብጽ ፣ ማላዊ እና ጊኒ ጋር የተደለደለች ሲሆን እስካሁን ሁለት ጨዋታ አድርጋ 3 ነጥብ በማግኘት በአንድ የግብ ክፍያ ምድቡን እየመራች ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!