የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኀበር ከሱዳን ተፈናቅለው በመተማ ዮሐንስ ከተማ ተጠልለው ለሚገኙ ወገኖች ከ4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ።

39

ገንዳ ውኃ: ሚያዝያ 26/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኀበር ከሱዳን ተፈናቅለው በመተማ ዮሐንስ ከተማ ተጠልለው ለሚገኙ 1ሺህ ዜጎች ከ4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኀበር አስታውቋል። በሱዳን በሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች በተፈጠረው ጦርነት ሸሽተው በርካታ ቁጥር ያላቸው የተለያዩ ሀገር ዜጎች በመተማ ዮሐንስ ከተማ ይገኛሉ። ለእነዚህ ተፈናቃዮችም የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኀበር ከአሁን በፊት 1ሚሊዮን ብር የሚገመት የተለያዩ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኀበር የሰሜን ጎንደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አታለል ታረቀኝ አስታውሰዋል።

አሁን ላይ የኢትዮጵያ ቀይመስቀል ማኀበር ከዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኀበር ጋር በመተባበር ለ1ሺህ አባውራ ተፈናቃዮች ከ4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የተለያዩ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ነው አቶ አታለል ለአሚኮ የተናገሩት። ከተደረጉ ድጋፎች መካከልም እንደ ሶላር፣ ሼራ፣ የምኝታ ምንጣፍ፣ የምግብ ማብሰያና ብርድ ልብስ በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው። እንደ አቶ አታለል ገለጻ ከሰብዓዊ ድጋፉ ባሻገር ዜጎችን በነጻ ስልክ በማስደወል ከቤተሰቦቻቸው ጋር የማገናኘት ተግባር እየተከናወነ ነው፤ እስካሁንም ከ5 መቶ በላይ ለሚኾኑ ዜጎች ነጻ የስልክ አገልግሎት መሥጠት ተችሏል። እየተደረገ ያለው ድጋፍ ከተፈናቃዮች ቁጥር ብዛት አኳያ በቂ አለመኾኑን የገለጹት አቶ አታለል ማኀበሩ እያደረገ ያለውን ሰብዓዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

ተፈናቃዮችም ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው በቀጣይ ሌሎች ረጅ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉላቸውም ጠይቀዋል። በሱዳን በተፈጠረው ጦርነት እስካሁን ከ50 በላይ ሀገራት የሚኾኑ ዜጎች ሸሽተው የኢትዮጵያ ድንበር ከተማ በኾነችው መተማ ዮሐንስ እየገቡ ሲኾን በቀን እስከ 1ሺህ ያህል ዜጎች እንደሚገቡ ተጠቁሟል።

ዘጋቢ፡- ቴዎድሮስ ደሴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!