የኢትዮጵያ ሳምንት ሊከበር ነው፡፡

0
49
የኢትዮጵያ ሳምንት ሊከበር ነው፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 26/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ለመጀመሪያ ጊዜ በሚከበረው የኢትዮጵያ ሳምንት እንደ ሀገር ያሉ እምቅ ሀብቶችን በአንድ ቦታ የሚታዩበት ትልቅ አውደ ርዕይ እንደሆነ ተነግሯል። በዚህ ኢትዮጵያ በአንድ ቦታ በምትታይበት አውደርዕይ ከሁሉም ክልሎች ተለቅመው የመጡ የባሕል፣ የታሪክ፣የተፈጥሮ እና የኢንቨስትመንት ጸጋዎች ለእይታ ይቀርባሉ፡፡
የኢትዮጵያ ሳምንት አብሮነትን እና ወንድማማችነትን ለማሳደግና ሀገራዊ ሀብቶችን ወደ ጥቅም ለመቀየር ፋይዳው የጎላ እንደሆነ የንዑስ ኮሚቴው አባል ኢንጂነር አይሻ ሙሀመድ ተናግረዋል። ለዚህ ትልቅ ሀገራዊ አውደ ርዕይ የተሳካ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከሁሉም የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ጋር የተናበበ መሪ እቅድ ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡ በዚህ አንድነትን ይበልጥ ለማሳደግ በተዘጋጀው መድረክ ኢትዮጵያ በኢትዮጵያውያን ትወከላለች ተብሏል፡፡ ሰዎችም እየተዝናኑ ኢትዮጵያን የሚያውቁበት ይሆናል።
በዕለቱም የኢትዮጵያውያንን ውስጣዊ አንድነት እና ውስጣዊ ትስስርን የሚያሳይ አዲስ ሙዚቃ ይመረቃል ተብሏል። ክልሎችም የተዘጋጀላቸውን ቦታ በአግባቡ እንዲጠቀሙ ተጠይቋል።
የዝግጅቱ ዓላማ በኢትዮጵያ ያሉ ሃብቶችን፣ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ማሳየት አብሮነትን ማሳደግ ይሆናል፤ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ውስጣዊ አንድነትን ማሳየት እንደሚገባም ተጠቅሷል፡፡ ከግብርና እስከ ኢንዱስትሪ ያሉን ሀብቶችን ማስተዋወቅ እና ኢትዮጵያን ከፍ አድርጎ ለማሳየት ያለመ ነው ተብሏል፡፡
አውደርዕዩ ቋሚ ለማድረግ እንደሚሠራ እና ኢትዮጵያን ወደ አንድ መንደር በማምጣት ቱሪስቶችን ለመሳብ ታስቦ የተዘጋጀ እንደሆነ የኮሚቴው አባል ዶክተር ሂሩት ካሳው አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ሳምንት አውደርዕይ አሴትም እሴትም ሆኖ እንዲቀጥል የራሱ የሆነ ሎጎም ተዘጋጅቶለታል ነው የተባለው።
ለአውደ ርዕዩ መግቢያ ለተማሪዎች 50 ብር ለአዋቂዎች ደግሞ 200 ብር ዋጋ ተቆርጦለታል። ከመግቢያ የሚሰበሰበው ገንዘብ በተለያዩ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች ማቋቋሚያ ይሆናል ተብሏል።
ዘጋቢ:– ጋሻው ፈንታሁን– ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here