የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለስልጣን ለዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ወረዳዎች የቢሮ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

65
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 13/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለስልጣን በዋግኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ለሚገኙት ለፃግብጂ እና ለአበርገሌ ወረዳዎች 6 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ ያገለገሉ ቋሚ የቢሮ ዕቃዎችን ድጋፍ አድርጓል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለስልጣን በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ተፈናቃይ ወረዳዎች ማለትም ለፃግብጂ እና ለአብርገሌ ያገለገሉ ቋሚ ዕቃዎች ድጋፍ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን ተወካይ አቶ ዮናስ ፋንታ፤ በሰሜኑ ጦርነቱ የተጎዱ እስካሁንም ድረስ በችግር ውስጥ ላሉ ለፃግብጂ እና ለአበርገሌ ወረዳዎች ቋሚ ዕቃዎችን በአይነት 50 ጠረጴዛ ፣ 17 የባለሞያ ወንበር ፣ 30 ደስክቶፕ ኮምፕዩተር ፣ 27 ላፕቶፕ ፣ 42 ፕሪንተር ፣ 18 ፎቶ ኮፒ ማሽን ፣ 4 ፋይል ካብኔት ፣ 9 ቴሌቭዥን ፣ 3 ቴሌቪዥን ማስቀመጫ ፣ 6 የውሃ ማጣርያ በጥቅሉ 6 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ድጋፍ መደረጉን ገልፀዋል።
አቶ ዮናስ አያይዘውም የአኹኑ የቢሮ ዕቃዎች ድጋፍ ለሕዝብ አገልግሎት ለሚሰጡ ተቋማት ነው። የድጋፉ ቀጣይነት ወረዳዎቹ ወደ አካባቢያቸው እስኪመለሱ እንዲሁም ከተመለሱ ብኋላ ለመልሶ መቋቋሙም የሚቀጥል ነው ። ሌሎች ተቋማትም እኛን አርዓያ አድርገው በዚህ ችግር ውስጥ ላሉ ወረዳዎች ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የፃግብጂ ወረዳ ገበያ እና ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ አደሩ ተሻለ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለስልጣን የተገኘው የአኹኑ ድጋፍ የፈርኒቸር እና የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች መኾኑ ለየት ያደርገዋል። ይህም ያለምንም ግብዓት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት ደፋ ቀና ለሚሉ ተቋማት ትልቅ ተስፋ ሰጭ እና አበርታች ነው ብለዋል።
አቶ አደሩ አክለውም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን በቀና አስተሳሰብ ተነሳስቶ ድጋፍ ከማድረጉ ባሻገር ደክመን ሰለቸን ሳይሉ እስከቦታው ድረስ ድጋፉን ይዞ በመምጣቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የፃግብጂ ወረዳ ገንዘብ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ አቶ ንጉስ ሙሉጌታ በበኩላቸው የቢሮ አገልግሎትን የሚያሳልጡ ቋሚ ዕቃዎች ድጋፍ ላደረገው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን እጅግ አመስግነው፤ ከደረሰብን ዘርፈ ብዙ ችግር አንፃር ድጋፉ ቀጣይነት እንዲኖረው ጠይቀዋል። መረጃዉ የጻግብጅ ወረዳ መንግሥት ኮምንኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ነዉ፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!