የኢትዮጵያ መንግሥት የድምበር ጉዳዩን በሠላማዊና ዲፕሎማሲያዊ አማራጭ ለመፍታት በቅድሚያ የሱዳን መንግሥት በኀይል የያዛቸውን ቦታዎች ለቆ መውጣት እንዳለበት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢፌዴሪ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ አስገነዘቡ፡፡

0
63
የኢትዮጵያ መንግሥት የድምበር ጉዳዩን በሠላማዊና ዲፕሎማሲያዊ አማራጭ ለመፍታት በቅድሚያ የሱዳን መንግሥት በኀይል የያዛቸውን ቦታዎች ለቆ መውጣት እንዳለበት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢፌዴሪ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ አስገነዘቡ፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 19/2013 ዓ.ም (አብመድ) በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢፌዴሪ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ አምባሳደሩ በወቅታዊና ሀገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ነው በኒውዮርክ፣ በኬኔቲኬት እና ኒውጀርሲ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ለሦስተኛ ጊዜ በዌብናር ውይይት ያደረጉት።
በውይይቱ አምባሳደር ታየ መንግሥት በትግራይ ክልል የወሰደው ህግን የማስከበር እርምጃ ከሕዝብ ሉዓላዊነት እና ከሀገር አንድነት ጋር ቀጥተኛ እንድምታ ያለው የህልውና ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል። በመሆኑም ህግን የማስከበር እርምጃው በስኬት ተጠናቆ ጊዜያዊ አስተዳደር በማቋቋም ሕዝቡ ወደ ተለመደው ሠላማዊ ኑሮው እንዲመለስ እየተደረገ እንደሆነ አብራተዋል፡፡
በክልሉ የመሰረተ ልማት አገልግሎቶች እየተጠገኑ ነው፤ በሠላም ማስከበሩ ሂደት የተፈናቀሉ እና ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችን ለመርዳት በኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ፣ በተ.መ.ድ.፣ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሰብዓዊ እርዳታ የማሰባሰብ እና እርዳታውን የማዳረስ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን በተመለከተ “ወገን ለወገን” የተሰኘ ድጋፍ አሰባሳቢ ግብረ-ኀይል ስለአከናወናቸው ተግባራት አምባሳደር ታዬ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ወረርሽኙ አሁንም የዓለማችን ብሎም የሀገራችን ከባድ የጤና፣ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ችግር ምንጭ እና ፈተና ሆኖ መቀጠሉንም ገልጸዋል።
ቋሚ መልዕክተኛው አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ የኮሮናቫይረስ ክትባትን ተደራሽ ለማድረግ በዓለም አቀፍ ንቅናቄ መጀመሩን ገልጸው ወረርሽኙን ለመግታት ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያና ሱዳን በወሰን ጉዳይ ላይ የነበራቸው የይገባኛል ጥያቄ ህጋዊና ሠላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት የጋራ የወሰን ኮሚሽን አቋቋመው ሲሰሩ እንደነበር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ አስታውሰዋል፡፡ ይህን የወሰን ጉዳይ ሁለቱን ሀገሮች በትብብር ለመሥራት ችግር ሆኖባቸው እንደማያውቅ ለተሳታፊዎች አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ በሱዳን በተከሰተው የፖለቲካ ችግር በሠላማዊ መንገድ እልባት አግኝቶ በሱዳን ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የኢትዮጵያ መንግሥት ግንባር ቀደም ሚና ተጫውቷል ብለዋል፡፡ በሱዳን በኩል ወቅታዊ የሀገራችን ሁኔታ እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ የወሰን ግፊት ማካሄዱ እጅግ አሳዛኝና የማይጠበቅ ተግባር እንደሆነም አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ጉዳዩን በሠላማዊና ዲፕሎማሲያዊ አማራጭ ለመፍታት ቅድሚያ መስጠቱንም አስረድተዋል፡፡ የድንበር ጉዳይ ሁለቱ ሀገራት ቀደም ሲል ባቋቋሟቸው የጋራ ድንበር ኮሚሽን፣ የቴክኒክ ኮሚቴዎች እልባት ሊሰጠው እንደሚገባ ወደ ድርድር መድረክ ለመቅረብ ግን የሱዳን መንግሥት በኀይል የያዛቸውን ቦታዎች ለቆ መውጣት ወይም ሁሉም ነገር ወደ ነበሩበት ሁኔታ መመለስ የግድ መሆኑን አብራርተዋል። ኢትዮጵያውያኑ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል። መረጃውን ያደረሰን በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ነው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here