የአድዋ ድል በውጭ ጋዜጦች!

97

የአድዋ ድል በውጭ ጋዜጦች!

ባሕር ዳር፡ የካቲት 23/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአድዋ ጦርነት ከ1880ዎቹ በምዕራቡ ዓለም ትልቅ ትኩረት ካገኙ ጉዳዮች አንዱ ነው። በዓለም ላይ የሚገኙ ጋዜጦች ስለጦርነቱ በርካታ ወቅታዊ ጽሑፎችን ተከታትለው በማውጣት ለአንባብያን አድርሰዋል።

ጋዜጦቹ በመጀመሪያ ገፃቸው ጭምር የአጼ የምኒልክንና የእቴጌ ጣይቱን ፎቶግራፍ በማውጣት የኢትዮጵያውያንን ጀግንነት ጎልቶ እንዲወጣ አድርገዋል፤ ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ ረገድም ትልቅ ድርሻ እንደነበረው ይነገራል።

ኒውዮርክ ታይምስ፣ ለ.ፔቲ ጆርናል የተባለ ፈረንሳይኛ ጋዜጣ እና ሀርፐርስ ዊክሊ ጋዜጦች ድሉን በሰፊው ከዘገቡት ውስጥ በግንባር ቀደም ተጠቃሾች ናቸው።

ጋዜጣዎቹ ስለጣይቱ ሲተርኩ ከምሥራቅ ኢጣሊያዊቷ ንግሥት ዜኖቢያ፣ ከግብፃዊቷ ንግሥት ክሊዎፓትራ፣ ከፈረንሳዊቷ ዝንድርክ እና ከሩሲያዊቷ ታላቋ ካትረን ጋር እያወዳደሩ ይዘግቡ ነበር።

የአድዋን ድል በተደጋጋሚ ከዘገቡት ጋዜጦች ኒውዮርክ ታይምስ አንዱ ነው። ጋዜጣው በአድዋው ጦርነት ዙሪያ በተለያዩ ጊዜያት የዘገባቸውን ከ50 ያላነሱ የዜና ሪፖርቶችን በምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ምስል አስደግፎ ነበር ያወጣው።

አይደፈርም ተብሎ የተገነባውን የመቀሌው ጠንካራ የጣሊያ ወታደራዊ የመከላከያ የጦር ሰፈር፣ የእቴጌ ጣይቱን እና የኢትዮጵያውያን ጀብደኞች በምስል አስደግፎ የዘገበው ሌላኛው ደግሞ የካሊፎርኒያው ጋዜጣ ይገኝበታል።

የሳንፍራንሲስኮ ጋዜጣም የአድዋ ድልን በጣሊያኖች ላይ የደረሰውን መሪር ሽንፈት “ሀበሾች አሸነፏቸው … የጣሊያ ወታደሮች በምኒልክ እጅግ ከባድ ሽንፈት ገጠማቸው… ካለቁት ውስጥ ጄኔራሎቹም…ይገኙበታል…” ወዘተ… በሚል ገልጾታል።

የሎሳንጀለስ ሄራልድ ጋዜጣ፣ ሀርፐርስ ዊክሊ የተባለው ሳምንታዊ መጽሔት እና ሌሎችም ጋዜጦች ጠንከር ካለ ዘገባቸው ጋር የጠላትን አንገት በጦርና ጎራዴ ለመበጠስ በጀግንነት ወደ ጠላት ምሽግ እየዘለሉ የሚገቡ የኢትዮጵያ ተዋጊዎችን፣ ከእቴጌ ጣይቱና አጼ ምኒልክ ምስል ጋር አውጥቷል።

የሀበሻን የጦር የዘመቻና የውጊያ እንቅስቃሴ ከጋዜጦች በተጨማሪ በመጽሀፍትም ይታተሙ ነበር።

ምንጭ፦ ንጉሴ አየለ ታላቁ ጥቁርና ጳውሎስ ኞኞ አጤ ምኒልክ

በዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
ዲስከቨር አማራ አሚኮ https://www.facebook.com/DiscoverAmharaAMECO
አሚኮ ስፖርት https://www.facebook.com/AMECOSport
አሚኮ መረጃ ማጣሪያ https://www.facebook.com/AMECOFactCheck