የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሀራ ገበያ የባቡር መስመር ፕሮጀክት በሁለቱም ዙር 90 በመቶ ሥራው ተጠናቋል ተባለ።

0
381

የባቡር ፕሮጀክቱ ከ4 ሺህ 800 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል።

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 02/2012 ዓ/ም (አብመድ) የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሀራ ገበያ የባቡር መስመር ፕሮጀክት ስላለበት ደረጃ አስተያየታቸውን ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት የሰጡት የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሀራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት የ‹ሴክሽን› ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሻሎም አሽሮ የባቡር መንገዱ አጠቃላይ ሥራ 90 በመቶ ተጠናቅቋል ብለዋል። ፕሮጀክቱ 390 ኪሎ ሜትር ይረዝማል። ከአዋሽ ኮምቦልቻ 270 ኪሎ ሜትሮች የሚረዝመው የመጀመሪያው ምዕራፍ 99 ነጥብ 6 በመቶ ሥራው መጠናቀቁን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

በአንደኛው ምዕራፍ የቅድመ ርክክብ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ የገለፁት ኢንጂነሩ የመጀመሪያው ምዕራፍ የርክክብና የሙከራ ሥራ ብቻ እንደቀረም ተናግረዋል። የመጀመሪያው ፕሮጀክት ለአገልግሎት ክፍት መሆን እንደሚችል በመግለፅ ከኮምቦልቻ-ሀራ ገበያ የሚሠራው የሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ 73 በመቶ ሥራው ተጠናቅቋል።

ርክክብና ሙከራ ለማድረግ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያስፈልጋቸውም ኢንጂነር ሻሎም ገልፀዋል። ፕሮጀክቱ ለኤሌክትሪክ አቅርቦት የሚያስፈልጉ ሥራዎችን ሁሉ እንደሠራ የተናገሩት እንጂነር ሻሎም የቀረው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅራቢ ተቋሙ ድርሻ እንደሆነም አመላክተዋል። ችግሩን ለመቅረፍ በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽንና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መካከል ምክክሮች እየተደረጉ እንደሆነ እና በቅርብ ጊዜ ይፈታል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።
መንግሥትም በኤሌክትሪክ ኃይል ዙሪያ ያለውን ጉዳይ ኃላፊነት ወስዶ እንዲሠራ ኢንጂነር ሻሎም ጠይቀዋል። እንደ ኢንጂነሩ ገለፃ በቅርቡ ቢያንስ ለሙከራ የሚሆን የኤሌክትሪክ ኃይል ከቅርብ እንዲለቀቅላቸው መግባባት ላይ መደረሱንም ገልፀዋል። ከኮምቦልቻ-ሀራ ገበያ የሚወስደው መንገድ ከካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ ችግር ገጥሞት እንደነበርና አሁን ላይ ችግሩ እየተፈታ እንደሆነም አስታውቀዋል።

ከተቋራጩ ጋር ያለው ቅንጅት መልካም መሆኑን ያነሱት ኢንጂነሩ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቱ ጉዳይ የሚዘገይ ከሆነ ግንኙነቱን ሊያሻክረው እንደሚችል አስታውቀዋል።

የባቡር ፕሮጀክቱ በ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚገነባ ነው። ፕሮጀክቱ በዚህ ወቅት ከ4 ሺህ 800 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። የአዋሽ-ኮምቦልቻ ሀራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት የካቲት 2007 ዓ.ም ነበር ግንባታው የተጀመረው። የባቡር ሀዲዱ 1 ነጥብ 435 ሜትር ‹ስታንዳርድ ጌጅ› ስፋት ያለውና ሙሉ ለሙሉ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠራ ነው። ፕሮጀክቱ በቱርኩ ዓለም አቀፍ ተቋራጭ ‹ያፒ መርከዚ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን› የሚሠራ ነው። መነሻውን አዋሽ አድርጎ መዳረሻውን ሃራ ገበያ የሚያደርገው የባቡር ፕሮጄክቱ 7 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው 65 ድልድዮች፣ 10 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው 12 ዋሻዎችና 827 የውኃ ማፋሰሻዎች አሉት። ስምንት የኃይል ማስተላለፊያና አስር የባቡር ጣቢያዎችም አሉት። ባቡሩ በሰዓት 120 ኪሎ ሜትር ይጓዛል። የባቡሩን አጠቃላይ ኦፕሬሽን ሥራና እንቅስቃሴ መቆጣጠሪያ ማዕከል በኮምቦልቻ ከተማ እየተገነባለት ነው። ግንባታው ሲጠናቀቅ 26 ባቡሮች ይኖሩታል። 20ዎቹ የዕቃ መጫኛ ስድስቱ ደግሞ የሕዝብ ማመላለሻ ይሆናሉ። አንዱ የሰው ማጓጓዣ ባቡር በአንድ ጊዜ 720 ሰዎችን ያጓጉዛል። ባቡሮቹ በቀን 4 ሺህ 320 ሰዎችን ማመላለስ ይችላሉ።

አንዱ የዕቃ ማመላለሻ ባቡር ደግሞ 1 ሺህ 350 ቶን የመሸከም አቅም አለው። አንዱ የዕቃ መጫኛ ባቡር 30 ተጎታቾች ይኖሩታል። አንዱ የዕቃ መጫኛ ባቡር 30 መኪኖች ከነተሳቢያቸው የሚጭኑትን ጭነት በአንድ ጊዜ የመሸከም አቅም አለው። የባቡር ትራንስፖርቱ አገልግሎት ሲጀምር ከአዋሽ ሀራ ገበያ ለመድረስ ከ4:30 እስከ 6:30 ይወስድበታል። ፕሮጀክቱ ወደ ጅቡቲ ወደብ ለመድረስ የሚወስደውን ጊዜ 50 በመቶ ይቃንሳል። ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ የሚዘረጋው የአፍሪካ የምድር ባቡር መረብ አካል የሆነው ይህ ፕሮጀክት ለመካከለኛውና ሰሜናዊ የኢትዮጵያ ቀጠና የኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይጠበቃል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here