ጎንደር :መጋቢት 11/2015 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ጌታቸው ጀንበር (ዶ.ር) እና ሌሎች የክልሉ የግብርና የሥራ ኀላፊዎች በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምዕራብ በለሳ ወረዳ የበጋ መስኖ ስንዴን እና የተፈጥሮ ሃብት ሥራን እየጎበኙ ነው።
ምክትል ርዕሰ መሥተዳደሩ በጉብኝታቸው ባለፉት ዓመታት በተፈጥሮ ሃብት ሥራ በተከናወኑ ተግባራት ለውጥ እየመጣ መኾኑን አረጋግጠናል ብለዋል።
ምክትል ርዕሰ መሥተዳደሩ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ ከመሥራትም ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲሰጥና ለወጣቶች የሥራ መስክ ማድረግም ይገባል ነው ያሉት።
በምዕራብ በለሳ የለማው የበጋ መስኖ ስንዴ ራስን መቻል እንደሚቻል ማሣያ ነው ብለዋል። በለሳ የበጋ መስኖ ስንዴ ለመጀመሪያ ጊዜ ማልማቱን የጠቀሱት ምክትል ርዕሰ መሥተዳደሩ” የአካባቢን ሃብት አውቆ ማልማት ከድኅነት ለመላቀቅ ብቻ ሳይሆን ተሰሚነትንም ማረጋገጥ ነው” ብለዋል።
በጉብኝቱ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኀላፊ ኀይለማርያም ከፍያለው (ዶ.ር) እና ምክትል ቢሮ ኀላፊዋ አልማዝ ጊዜው(ዶ.ር) በበጋ መስኖ ስንዴና በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ የተገኙ ውጤቶችን አጠናክሮ እንዲሁም ጉድለቶችን አስተካክሎ ለመሔድ መተባበር ያስፈልጋል ብለዋል።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን 13 ሺህ 850 ሄክታር ማሣ በስንዴ መልማቱን ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ዘጋቢ፡- አገኘሁ አበባው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!