“የአንድነትን ዋጋ፣ ክብርና ገጽታን አለመረዳት ልዩነትን ያሰፋል” የፍልስፍና መምህር ጠና ደዎ (ዶ.ር)

56

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 12/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያውያን ነጻነታቸውን ያስከበሩባቸው፣ ጠላቶቻቸውን የቀጡባቸው፣ ችግሮቻቸውን የፈቱባቸው፣ ዘመናትን የተሻገሩ እሴቶች አሏቸው፡፡ እሴቶቻቸው የመከራ ቀን መወጣጫ መሰላል እየሆኑ አሻግረዋቸዋል፡፡ በአንዲት ሀገር በአንድ ሠንደቅ ሥር አኑሯቸዋል፡፡ የከበሩ እሴቶቻቸው እና ለእሴቶቻቸው ያላቸው ክብርና ፍቅር በታሪክ ውስጥ ጎላ ብለው እንዲጻፉ ያስቻሏቸውን ጀብዱዎች እንዲፈጽሙ አድርጓቸዋል፡፡

ልዩነቶቻቸውን እንደጌጥ ተጠቅመው፣ በአንድ ሠንደቅ ሥር ተውበው፣ በአንዲት ሀገር ጣሪያ ሥር ደምቀው ኖረዋል፡፡ እየኖሩም ነው፡፡ የጠነከሩ እሴቶቻቸው የጠላትን የጦር ፍላጻ መልሰው፣ በድል እና በኩራት እንዲኖሩ አድርገዋቸዋል፣ ለከበሩት እሴቶች ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ዙፋን ላይ የሚቀመጡት መሪዎችም ልዩ አክብሮትና ትኩረት ይሰጧቸዋል፡፡ የሀገር መሠረቱ የጋራ እሴት እና አንድነት እንደኾነ በውል ይረዳሉና፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ለጋራ እሴቶች የሚሰጡ ግምቶች ማነስና መልካም የሆኑ ጉዳዮች መድከም ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን ሲፈትኗቸው ይስተዋላል፡፡

በአዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር ጠና ደዎ (ዶ.ር) የትኛውም ማኅበረሰብ የራሱ የኾነ እሴት አለው፣ እሴት ጥልቅ ነገሮችን የያዘ ውስብስብ ጉዳይ ነው፡፡ ማኅበረሰቦች የእኔ የሚሏቸውና የጋራ የሚላቸው እሴቶች አሏቸው፡፡ የጋራ የኾኑ እሴቶች አንደኛው ሌላኛውን በቀላሉ ለመረዳት፣ ለመረዳዳትና በአንድነት ለመኖር ያስችላል ነው የሚሉት፡፡

ኢትዮጵያውያን በጥንካሬ የሚነሱባቸው ብርቱ እሴቶች አሏቸው ያሉት ዶክተር ጠና፤ እሴቶቻቸው በአንድነት ቆሞ ሀገርን የመጠበቅ፣ ሀገርን የመንከባከብ እድል እንደሰጧቸውም ገልጸዋል፡፡ የጋራ እሴቶች ሀገር እንድትቆይ፣ ሀገር እንዳትደፈር ፣ በነጻነት እንድትጸና አድርገዋልም ነው ያሉት፡፡

እሴት በቀላሉ ሊነገር የሚችል ጉዳይ አይደለም፣ ረቂቅ እና ውስብስብ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ጠላቶቻቸው በውል ያልተረዱት፣ በኢትዮጵያ ላይ ክፉ የሚያስቡና የሚያደርጉ ያላወቁት ረቂቅ የኾነ እሴት አለ፡፡ ያ ረቂቅ እሴትም ተበተኑ ሲባሉ ይሰበስባቸዋል፣ ተሸነፉ ሲባሉ ባለ ድል ያደርጋቸዋል፣ ከብዙ ሀገራት ለይቶም በነጻነት አቆይቷቸዋል፡፡

እሴትን እንደ ቁሳቁስ መለካት አይቻልም የሚሉት ምሁሩ በሕይዎት ሂደት ውስጥ ግን የእሴት መዳከምን እና መበርታትን ማየት ይቻላል ይላሉ፡፡ በኢትዮጵያ የነበረው ጦርነት፣ መገዳደል፣ መሳደድና የጥላቻ ስሜት እሴቶቻችን የተዳከሙ መኾናቸውን ያሳዩናል፣ ነገር ግን ጠፍተዋል፣ ማለት አያስችለንም ምክንያቱም እሴት ውስብስብ ስለሆነ ነው ያሉት፡፡ በቅርብ ጊዜ በኢትዮጵያ የታዩና እየታዩ ያሉ ጭካኔዎች፣ ጥላቻዎች፣ አብሮ የመኖር መላላት የእሴቶች መዳከም ያሳዩናል ነው ያሉት፡፡

አብሮ የመኖር፣ የመደማመጥ፣ የመተሳሰብ እና የመተጋገዝ እሴቶች ሲዳከሙ ቂም፣ ጥላቻ ፣ ጭካኔ እንደሚመጣም ተናግረዋል፡፡ ጭካኔዎች እና ጥላቻዎች አንዱ ለሌላኛው ተገቢው ፍቅርና ክብር ካለመስጠት የሚመጡ መኾናቸውን ነው የተናገሩት፡፡ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ከእሴቶች መዳከምና መቀዛቀዝ ጎን ለጎን እሴቶችን ለማጎልበት የሚደረጉ ጥረቶች መኖራቸውንም ዶክተር ጠና ያነሳሉ፡፡ ለአብነት የሚያነሷቸው ደግሞ ከዚህ በፊት የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶች፣ ሀገራዊ የኾኑ የጋራ ፕሮጄክቶች መኖርና ለጋራ ፕሮጄክቶቹ በጋራ መነሳት ናቸው፡፡ እነዚህ ደግሞ እሴቶቻችንን እንደገና ለማጠናከር የሚያግዙ ናቸው ነው ያሉት፡፡ በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ እሴት ፈርሷል፣ ተዳክሟል፣ ጠፍቷል ማለት እንደማይቻልም ገልጸዋል፡፡

የአንድነትን ዋጋ፣ ክብርና ገጽታ አለመረዳት ልዩነትን እንደሚያሰፋም አስረድተዋል፡፡ የተለያዬ ባሕል፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋና ወግ ባለባት ሀገር ላይ ልዩነትን ማጥፋት አይቻልም፣ የሚቻለው ልዩነትን ማስታረቅ ነውም ብለውኛል፡፡ ልዩነትን ማስታረቅ የሚቻለው ደግሞ አዕምሮ ላይ በመሥራት እንጂ፣ በጉልበት አይደለም ነው ያሉት፡፡ መደማመጥ፣ ስለታጣ፣ ልዩነት በጣም ግዝፎ አንድነት እንዲመነምን እና እንዲዳከም ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡

አንደኛው ከሌለ ሌላው መኖር አይችልም የሚሉት ዶክተር ጠና፤ አንድነታችን ውስጥ ምንም አይነት ችግር እንዳይፈጠር ከተፈለገ ልዩነታችንን በሚገባ ማስተዳደር፣ መረዳት እና መቆጣጠር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ልዩነትን ለማስተዳደር እና ለመቆጣጠር በሰከነ መንፈስ መነጋገር እና መደማመጥ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል፡፡

ምን ያክል ነው የምንለያየው? ልዩነቱስ ምን ችግር ፈጠረብን? በልዩነቶቻችን መጠቃቀም ስንችል፣ ለምንድን ነው ልዩነትን መኾን ከሚገባው በላይ አግዝፈን አንድነታችንን የምናኮስሰው? በሚል በመወያየት ችግሮችን መቅረፍ ይቻላል ነው ያሉት፡፡ ሁልጊዜም ችግር የሚከሰተው የማንወያይ መሆናችን እና ሀሳብን የምንፈራ በመሆናችን ነውም ብለዋል፡፡ችግርን በመፍራት ወደ ማይፈለግ አካሄድ እንደሚኬድም ገልጸዋል፡፡ መጥፎ አካሄድን ያለፈው ጥሎት ሲሄድ የሚከተለውም እዛው ጉድጓድ ውስጥ ይገባል፣ አይነቱን አይለውጥም፣ እኩይን ሥራ መቀባበል አያስፈልግም ነው ያሉት፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ አንድነትን እና ልዩነትን መረዳት ቀላል ነው ያሉት ዶክተር ጠና፤ በልዩነትም በአንድነትም መጠቀም እንደሚቻል ነው የተናገሩት፡፡ ልዩነትን በአግባቡ መያዝ እና ማስተዳደር በእጅጉ ይጠቅማል ነው ያሉት፡፡ ልዩነትን ማስተዳደር የሚያስችል ጥበብ እጃችን ላይ አለ፣ ያቃተን መጠቀሙ ላይ ነውም ብለዋል፡፡

ዛሬ በዓለም ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ የኾኑ ሀገራት በችግሮች ውስጥ አልፈው ከከፍታ የደረሱ መኾናቸውን የተናገሩት ዶክተር ጠና፤ ችግር ሁሌም ይኖራል፣ ለከፋ ነገር የሚዳርገው ግን ችግርን የመፍታቱ ሂደት ነው ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ተቋማዊ የኾኑ ሥራዎች እየተሠሩ አለመኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ሥራዎች እና እንቅስቃሴዎች ቡድኖችን እና ግለሰቦችን መሠረት ያደረጉ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ የቡድኖች እና የግለሰቦች እንቅስቃሴ ችግር ሲገጥም ሁሉም ነገር ይፈራርሳል፣ ይህ መሆኑ ቀርቶ ቋሚ የሆነ ተቋም እና ተቋማዊ አደረጃጀት ፈጥሮ የሚከሰቱትን ችግሮች በተቋማዊ አደረጃጀት አቅም መፍታት ይገባልም ነው ያሉት፡፡

ችግሮቻችንን በዘላቂነት ለመፍታት ተቋሚ ሥራዎች ላይ ማተኮር ይገባልም ነው ያሉት፡፡

ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!