የአንዳቤት ወረዳ ሚሊሻ አሸባሪውን የትህነግ ቡድን ለመደምሰስ የሚካሄደውን የህልውና ዘመቻ ለመቀላቀል ወደ ግንባር አቀና፡፡

0
158

የአንዳቤት ወረዳ ሚሊሻ አሸባሪውን የትህነግ ቡድን ለመደምሰስ የሚካሄደውን የህልውና ዘመቻ ለመቀላቀል ወደ ግንባር አቀና፡፡

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 01/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር ዞን የአንዳቤት ወረዳ ሚሊሻ አሸባሪውን የትህነግ ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ የሚደረገውን የህልውና ዘመቻ ለመቀላቀል ወደ ግንባር ዘምቷል፡፡

የአንዳቤት ወረዳ የሥራ ኀላፊዎች እና ነዋሪዎች ለሚሊሻ አባላት አሸኛኘት አድርገውላቸዋል፡፡ በሽኝት ሥነ ሥርዓቱ ያነጋገርናቸው ዘማች የሚሊሻ አባላት እና ሸኚዎች አሸባሪው ትህነግ እስኪደመሰስና ኢትዮጵያ ሰላሟን እስክታገኝ ድረስ በሁለም ዘርፍ ያለረፍት እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

ሚሊሻ ደሴ እሱባለው በሰጡት አስተያየት አሸባሪው ትህነግ ፍላጎቱ ኢትዮጵያን ማተራመስ ስለኾነ ይህንን ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አስወግደን ወደ ሰላማችን እንመለሳለን፤ ይህንን ለማድረግም ወደ ግንባር በመዝመትና ያልዘመተው ደግሞ በአቅሙ በመደገፍ አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡

ሚሊሻ እንዳየሁ አዲስ በበኩላቸው አሸባሪው ትህነግን ደምስሰን ኢትዮጵያን ሰላም ለማድረግ ሁላችንም መዝመት አለብን፤ በፌስ ቡክና በሌሎች የማኅበራዊ ትስስር ገጾች የሚለቀቀው የሐሰት መረጃና ውዥንብርም ሕዝቡን ሊያደናግር አይገባም ነው ያሉት፡፡

የወረዳው ሕዝብ ገንዘብ እና ስንቅ በማሰባሰብ ለሚዘምተው ሚሊሻ ደጀንነቱን እያሳየ ነው፤ ቤተሰቦቻቸውንም በመንከባከብና ያሉ ሥራዎችን በመሥራት ኢትዮጵያን ሰላም ለማድረግ በሚካሄደው ትግል የበኩሉን እየተወጣ እንደኾነ ነው ዘማች ሚሊሻ እንዳየሁ የነገሩን፡፡

የአንዳቤት ወረዳ ነዋሪ ሃምሳ አለቃ አስናቀ ታረቀኝ የህልውና ዘመቻውን ሕዝቡ በገንዘብ፣ በሞራልና በቁሳቁስ እንዲሁም የዘማች ቤተሰቦችን በገንዘብና በእርሻ ሥራ እየደገፈ ነው ብለዋል። እርሳቸውም ሚሊሻ በማሰልጠን የሚጠበቅባቸውን እየተወጡ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

አርሶ አደር አስናቀ አድማሱ ስንቅና ትጥቅ በማቅረብ፣ አካባቢን በመጠበቅ፣ የዘማች ቤተሰቦችን የመንከባከብ ሥራ እየሠሩ መኾኑን ነው የነገሩን፡፡ ወደ ግንባር በመዝመት የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

“ለመዝመት ዝግጁ ነኝ፤ ሴቶች ሚሊሻውንና ወጣቱን እያበረታታን እንዲዘምቱ እያደረግን ነው፤ ለዘማቹ በስንቅ ዝግጅትና አቅማችን የፈቀደውን ያክል እየሰጠን ነው” ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ብርቄ አየልኝ ናቸው፡፡

ስንቅ በማዘጋጀት፣ የዘማች ቤተሰቦችን እያበረታታንና እየደገፍን ነው ያሉት ወይዘሮ ብርቄ በሁለም ሥራ እየተረዳዳን የህልውና ማስከበር ዘመቻው በድል እንዲደመደም እየተጋገዝን ነው ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ – ከአንዳቤት

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m