“የአንቶኒ ብሊንከን ጉብኝት የአሜሪካ እና የኢትዮጵያን ግንኙነት ወደ አዲስ ምእራፍ መሸጋገሩ ማሳያ ነው” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

54
አዲስ አበባ: መጋቢት 07/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን በሁለትዮሽ እና ሌሎች ቀጣናዊ ግንኙነት ላይ ረዘም ያለ ውይይት ስለማድረጋቸው የመስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ አለም በሳምንታዊ መግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የፕሬዚዳንታቸውን ደብዳቤ ይዘው 3 ጉዳዮች ላይ አላማ ያለው ጉብኝት ስለማድረጋቸው ተናግረዋል። በዚህ በቀጣናዊ፣ የሁለትዮሽ እና የኢትዮጵያ የሰላም ጉዳይን በመደገፍ ጠንካራ ግንኙነትን ለመፍጠር ያለመ ነው ብለዋል።
የአሜሪካ መንግሥትም 331 ሚሊዮን ዶላር ለኢትዮጵያ እንደሚረዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መናገራቸውንም አስገንዝበዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባዩ አምባሳደር መለስ ጉብኝቱ እና ውይይቶች ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ወደ አዲስ የግንኙነት ምእራፍ ስለመሸጋገራቸው የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል። የኢትዮጵያን የሰላም ጉዳይ አሜሪካ እንደምትደግፍ መናገራቸውንም ቃል አቀባዩ ጠቅሰዋል።
አልሻባብ የአሜሪካ፣ የሶማሊያ፣ የኢትዮጵያ እና የቀጣናው ጠላት በመኾኑ ቡድኑን ለማጥፋት የሚደረግ ጥረትን አሜሪካ እንደምትደግፍና የሶማሊያ ተቋማትን እንደምታጠናክር ብሊንከን ስለመናገራቸው አብራርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሳምንቱ በደቡብ ሱዳን ያደረጉት ጉብኝት ዲፕሎማሲን ያጠናከረ እና በደቡብ ሱዳን በሪክ ማቻር እና በሳልቫኪር ማያርዲት ያለው ልዩነት በሰላም እንዲፈታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለማግባባታቸው ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- አንዱዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!