የአሸባሪው ትህነግን የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ሰምተው እና ተገደው ወደ ጦርነት የገቡ የትግራይ ሕጻናት እና ወጣቶች በሰላም እጃቸውን እንዲሠጡ በማይጠብሪ ግንባር የተማረኩ የሽብር ቡድኑ አባላት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

0
247
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 14/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአሸባሪው ትህነግን የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ሰምተው እና ተገደው ወደ ጦርነት የገቡ የትግራይ ሕጻናት እና ወጣቶች በሰላም እጃቸውን ለሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻና ፋኖ እንዲሠጡ በማይጠብሪ ግንባር የተማረኩ የሽብር ቡድኑ አባላት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አሸባሪው የትህነግ ቡድን አማራን እንዲገሉና እንዲዘርፉ ስልጠና ተሰጥቷቸው በማይጠብሪ ግንባር የተሠለፉ በርካታ የቡድኑ አባላት እየተደመሰሱ ይገኛሉ። ጥቂቶቹ ከወገን ጦር በተሰነዘረባቸው ከባድ የማጥቃት እርምጃ ተደናግጠው እየተበታተኑ ነው። ቀሪዎችም በመከላከያ ሠራዊት፣ በአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻና ፋኖ ተማርከዋል፡፡
አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ያነጋገራት ምርኮኛ ነፃነት ሰይፈ ለአቅመ ውትድርና ሳትደርስ አሸባሪው ትህነግ አማራን ለማጥፋትና ኢትዮጵያን ለማፈራረስ በጀመረው ውጊያ ተሠልፋ ተማርካለች። እንደ ምርኮኛዋ ገለፃ ከአሸባሪው ትህነግ ከአማራ ክልል ኮምፒውተር፣ መኪና እና የተለያዩ የቤት ዕቃዎችን በመዝረፍ ትግራይ እንዲወስዱ ተልዕኮ ተቀብላለች።
የመምህር ልጅ መሆኗን የገለጸችው ነፃነት ወደ ውጊያ ከመሠማራቷ በፊት በአክሱም ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ነበረች። አሸባሪው ትህነግ ጎንደር፣ ባሕር ዳር፣ አዲስ አበባን እንቆጣጠራለን በማለት ወደ ግዳጅ እንዳሰማራት ተናግራለች።
የተወሰነ ደረቅ ብስኩት ብቻ በመያዝ ወደ በረሃ እንድትወርድ መደረጓንም ጠቅሳለች። ከአጭር ቀን ስልጠና በኋላ በግንባሩ በነበረ አንድ ሻለቃ ውስጥ ሆናም በዕድሜያቸው አቻ ካልሆኑ የአሸባሪው ትህነግ አባላት ጋር የስለላ ተግባር እንድትፈጽምም ተነግሯት ነበር።
ከአሸባሪው ትህነግ የሚሰጣቸው ስልጠና ትኩረቱ እንዴት አማራን መግደል፣ ሃብትና ንብረት መዝረፍ፣ ቤትና መሰል ንብረቶችን ማቃጠል እንደሚቻልና እነሱ ያልመሯት ኢትዮጵያ እንዳትኖር ለማድረግ መሆኑን አብራርታለች።
እንዲህ ዓይነት ጭቃኔ የተሞላበት ሥራ እንዲሠሩ ደግሞ ወደ ውጊያው ከመግባታቸው በፊት መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና የኤርትራ ሠራዊት በትግራይ ሕዝብ ላይ በደል አድርሷል በማለት አሸባሪው ትህነግ የውሸት ፊልሞችን ሰርቶ እንዳሳያቸው አብራርታለች።
ሕጻናትን በማያውቁት አጀንዳ በማስገባት ከትምህርታቸውና ከቤተሰቦቻቸው የነጠለው አሸባሪው ትህነግ በደል መሥራቱን ምርኮኛዋ ተናግራለች። ከተማረከች በኋላ አሸባሪው ትህነግ የነገራት ነገር በሙሉ ውሸት መሆኑን የተረዳችው ነፃነት የትግራይ ሕፃናት ከጦርነት ወጥተው ኢትዮጵያዊነትን መላበስ ይፈልጋሉ፤ ከጫፍ እስከ ጫፍ ካለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አብሮ መኖር ይናፍቃሉም ስትል ገልጻለች።
ሌላው ምርኮኛ አብዱልቃዲር ያሲንም የአክሱም ከተማ ነዋሪ ነበር። ከዚህ በፊት በመኪና ረዳትነት ሲሠራ እንደነበር ነግሮናል። በሥራ ምክንያትም ጎንደር እና ባሕር ዳርን ከአሁን በፊት ያውቃቸዋል። አሸባሪው ትህነግ በግዳጅ ለጦርነት እንዲሰለፍ እንዳደረገው ተናግሯል። “ወደ ጦርነቱ ስገባ ደስተኛ አልነበርኩም” ያለው አብዱልቃዲር እጅ በመስጠቱ ከአሸባሪው ትህነግ እንግልት ማረፉንም አስረድቷል።
ለትግራይ ልጆች ትምህርት ቤት የሠራውንና የተለያዩ ድጋፎችን ያደረገውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት በጨለማ ጥቃት የፈጸመው አሸባሪው ትህነግ ለትግራይ ሕዝብም ምንም እየጠቀመ አይደለም ብሏል ምርኮኛው፡፡ ወደ ውጊያው የገቡ የትግራይ ሕጻናት እና ወጣቶች ለመንግሥት የጸጥታ አካላት በሠላም እጅ በመስጠት ከጥፋት እንዲታቀቡ ጥሪ አቅርቧል።
አሸባሪው ትህነግ በተለይ በአክሱም የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ነዋሪዎች ላይ ሲፈጽም የኖረው ግፍ የማይረሳ መሆኑንም አንስቷል፡፡ ለጦርነት ሲሆን ሁሉን እያስገደደ እያጋፈጠ መሆኑን ነው ያስረዳው፡፡ ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ እየተደረገለት ባለው እንክብካቤ እንደተረዳው አብዱልቃዲር የአማራም ሆነ ሌላው ሕዝብ ወንድም ሕዝብ እንጂ ጠላት አይደለም ብሏል።
አሸባሪው ትህነግ በአሁኑ ወቅት ሕጻናትን በሀሺሽ በማደንዘዝ ወደ አውደ ውጊያ እየማገደ መሆኑን አጋልጧል።
ሌላው የጦር ሜዳ ምርኮኛ ተማሪ ምናለ መኮንንም የአክሱም ከተማ ነዋሪና የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ነበር። በኮልታፋ የአማረኛ ንግግር አንደበቱ ብዙ የትግራይ ሕጻናት በማያውቁት መንገድ ወደ ጦርነት በመግባት ከባድ ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን ተናግሯል። እሱም እጅ በመስጠቱ ሕይወቱን ማዳኑን ገልጿል። ሌሎችም የቡድኑ አባላት በሰላም እጅ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርቧል።
ዘጋቢ:- አዳሙ ሽባባው- ከማይጠብሪ ግንባር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here