የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ በደሴ ከተማ ለተጠለሉ ተፈናቃይ ወገኖች የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

0
119

ደሴ: ጳጉሜን 01/2013 ዓ.ም(አሚኮ)በአሸባሪው የትህነግ ወራሪ ኀይል ተፈናቅለው በደሴ ከተማ ለተጠለሉ ወገኖች የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸውን የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ ለወሎ ዩኒቨርሲቲ አስረክቧል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የተደረገለትን የድጋፍ ጥሪ ተቀብሎ ድጋፍ ያደረገ 12ኛው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ነው።

በሽብርተኛው የትህነግ ወራሪ ኀይል ለተፈናቀሉት ወገኖች አጋርነታቸውን ለማሳየት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸውን 700 ብርድልብስ፣ 50 ኩንታል ፍርኖ ዱቄት እና ከ400 በላይ አንሶላዎችን በድጋፍ ለወሎ ዩኒቨርስቲ ማስረከባቸውን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ገዝሙ ቀልቦ ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው ከኢትዮጵያውያን ጎን በመቆም ቀጣይነት ያለውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ስልጠና ዳይሬክተርና የእርዳታ አሰባሳቢ ግብረኀይል ኮሚቴ አባል ዶክተር ጌታቸው ጉግሳ ድጋፉ ዩኒቨርሲቲዎች ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን ለወገን አለኝታነታቸውን በተግባር ያሳዩበት እንደመሆኑ ሌሎችም ዩኒቨርስቲዎች የሚያደርጓቸውን ድጋፎች አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በኩል ለተደረገው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞች ለተፈናቃዮች ካደረጉት ድጋፍ ባለፈ ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ ለመከላከያ ሠራዊት በመደገፍና ደም በመለገስ አጋርነታቸውን እንዳሳዩም ተገልጿል።

ዘጋቢ:- ቤተልሄም ሰለሞን

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m