የአሜሪካን መንግሥት ማእቀብ በመጣል የኢትዮጵያን እጅ ለመጠምዘዝና ተንበርካኪ መንግሥት ለመፍጠር የሚያደርገውን ሴራ ለመቋቋም በአንድነት መቆም እንደሚገባ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ ገለጹ፡፡

0
105

መስከረም 09/2014 ዓ.ም (አሚኮ) “አንድ ሺህ እራት ለዓባይ ግድብ” በሚል በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ በዩናይትድ ኪንግደም እና አየር ላንድ የህዳሴ ግድብ አስተባባሪ ኔትዎርክ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በመጪው ጥቅምት 9/2021(እአአ) ለንደን ላይ የሚካሄደው ታላቅ የገቢ ማሰባሰበያ ዝግጅት ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው በአንድነት ስለመቆማቸው ማረጋገጫ ነው ብለዋል፡፡

በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ የሌላን ሀገር ጥቅም የመጋፋት ፣ ጣልቃ የመግባትና የመውረር ታሪክ የሌላት ሀገር ናት፡፡ የሌሎችን ጥቅም በማክበር ነጻነቷንና የራሷን ጥቅም በማስከበር ለሀገሮች ሰላም፣ ብልጽግናና መረጋጋት አበክራ ትሠራለች ነው ያሉት፡፡

አምባሳደሩ በየጊዜው ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን እና የውጪ ጫናዎችን በመቋቋም የህዳሴ ግድቡን ወደማጠናቀቂያ ምእራፍ ላይ ማድረሰ መቻሉን አስረድተዋል፡፡
ከሰሞኑ እየተቃጣብን ያለው እጅ የመጠምዘዝ ሙከራ ዘላቂ እልባት የሚያገኘው በዜጎች ትብብር ግንባታውን ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ነው ብለዋል፡፡

ሽብርተኛው ትህነግን ሙሉ የሕዝብ ድምጽ አግኝቶ ከተመረጠ መንግሥት እኩል ለመፈረጅ የሚደረገው ሙከራ ተቀባይነት የለውም ነው ያሉት አምባሳደሩ፡፡

በአማራና አፋር ክልሎች ሽብርተኛው ትህነግ የፈጸመውን ኢሰብአዊ ድርጊት፣ የዜጎች ሞት እና መፈናቀል የአሜሪካን መንግሥት እንዳላሳሰበው ጠቅሰዋል፡፡

ለኢትዮጵያ ህልውና ከዜጎቿ ውጪ ማንም ደራሽ እንደሌለ በመገንዘብ በዩናይትድ ኪንግደምና አየርላንድ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከመንግሥትና ከሕዝብ ጎን በመቆም የህዳሴ ግድብን ለማጠናቀቅ በሚደረገው ጥረት አንድነታቸውን ይበልጥ በማሳየት እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሀገር ውስጥ ያለው ሕዝብ ህይወቱን ለሀገሩ እየሰጠ ያለበት ወቅት መሆኑን አምባሳደር ተፈሪ ጠቅሰዋል፡፡

በውጪ ሀገር ነዋሪ የሆነው ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሌላ አማራጭ ሀገር የሌለው በመሆኑ ለሀገሩ ሰላም፣ አንድነትና ብልጽግና በነቂስ ወጥቶ በመጪው ጥቅምት 9/2021 (እአአ) ለንደን ላይ በመገኘት ድጋፉን እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

በዩናይትድ ኪንግደም እና አየር ላንድ የህዳሴ ግድብ አስተባባሪ ኔትዎርክ ሊቀመንበር አቶ መንግሥቱ ጃብር በበኩላቸው “የጨለማን ዘመን ሸሽተን ነው ከሀገር የተሰደድነው፤ ተመልሰን ወደጨለማ እንዳንገባ ኢትዮጵያን የመቀየር ኀላፊነት በትከሻችን ላይ አርፏል፤ ማንንም ተስፋ አድርገን ልንኖር አይገባም” ብለዋል፡፡

“የውጪ ሀገር ፓስፖርት ሊሻር ወይንም ሊቀየር የሚችል ነው፤ ኢትዮጵያዊነት ግን ማንም ሊሰጠን ወይንም ሊሽረው የማይቻለው በተፈጥሮ የተሰጠን መለያ ፓስፖርታችን ነው” ያሉት አቶ መንግሥቱ ሀገራችንን የመገንባት ግዴታ የእኛ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከኢትዮጵያዊያን በላይ ለኢትዮጵያ የሚደርስ ባለመኖሩ በመጨው ጥቅምት 9/2021 በሚካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት በመገኘት የዜግነት እና የኢትዮጵያዊ ግዴታችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

አቶ መንግሥቱ የህዳሴ ግድብ የሉዓላዊነታችን እና የአንድነታችን መገለጫ በመሆኑ ሉዓላዊነታችንንና አንድነታችንን ሊዳፈር የመጣውን ኃይል በምንመክትበት መጠን የህዳሴ ግድባችንን ልንጠብቅ በገንዘብ በመደገፍ ግንባታውን አጠናቀን ከጨለማ ዘመን ልንወጣ ይገባል ነው ያሉት፡፡

በዩናይትድ ኪንግደም የዩናይትድ ኢትዮጵያ ሊቀመንበር ልኡልሰገድ አበበ (ዶ.ር) በበኩላቸው የህዳሴ ግድብ እንደሌሎቹ የኢትዮጵያ ቅርሶች የዚህ ዘመን ትውልድ ለመጪው ትውልድ የሚያስተላልፈው ቅርስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከኃይል ማመንጨት ጀምሮ ለሁለንተናዊ እድገታችን ምልክት ፣ ዜጎቻችንን ከስደት እና ከጨለማ ኑሮ ለማውጣት ተስፋን የሰነቅንበት ነው ብለዋል፡፡

ዶክተር ልኡልሰገድ ❝በተለይም በአሁኑ ወቅት የአሜሪካን መንግሥት ጭፍን የሆነ የኢኮኖሚ ጉዳት ለማድረስ እና ጉዞአችንን ለመግታት እየተንደረደረ ባለበት ወቅት ከፍታችንን በመጠበቅ እና አንድነታችንን ይበልጥ በማጠናከር ወደብልጽግና የምናደርገውን ጉዞ ስኬታማ ማድረግ ይገባል❞ ነው ያሉት፡፡

ለግድቡ ግንባታ በዩናይትድ ኪንግደም እና ሰሜን አየር ላንድ ነዋሪ በሆኑ ዜጎች ትብብር “itsmydam.et” በሚል ለስጦታ በተከፈተ ድረ ገጽና መተግበሪያ በአጭር ጊዜ ከአንድ መቶ ሰላሳ ሺህ ዶላር በላይ መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡
ምንጭ፡- በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m