“የአማራ ክልል በሚገባው ልክ እንዳያድግ ያደረገው በኃይል አቅርቦት ላይ የተሠራው መዋቅራዊ ሥራ ነው” የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል

0
87
ባሕር ዳር፡ ሕዳር 17/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል እንደገለጹት፤ ቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርክ የኃይል አቅርቦቱ እንዲፈታ ከፍተኛ ጥረት ተደርጎ አሁን ተስፋ ያለው ሂደት ላይ ነው።
በአማራ ክልል ከጦርነት ማግስት ሕዝቡ የሚያነሳውን የመልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ እየተሰጠ ያለው ጠንካራ እና የተቀናጀ አመራር የሚመሰገን ነው ብለዋል።
እውቀትና ክህሎት ያልተጨመረበት የግብርና ሥራ ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ሊገነባ አይችልምና እሴት የተጨመረበት ምርት ለገበያና ለተጠቃሚ ለማቅረብ ባለሃብቶችን ይፈልጋል ነው ያሉት።
አልሚ ባለሃብቶች ዝግጁ በኾነው በቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ገብታችሁ እንድታለሙ ተጋብዛችኋል ብለዋል።
ኢንዱስትሪ ፓርኮች የሥራ እድል በመፍጠር፣ ለአርሶ አደር ምርትን ገበያ በመኾን፣ ለአልሚው ባለሀብትም የት ሂጀ ላልማ የሚለውን ጥያቄ የመለሱ ናቸው ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት የአግሮ ኢንዱስትሪዎች በመስፋፋታቸው አነስተኛ ምርት የሚያመርቱ አርሶ አደሮችን ጨምሮ የማምረት አቅም እንዳሳደገ ነው የተናገሩት።
“የአማራ ክልል እንዳያድግ ዋናው ችግር በመሠረተ ልማት በተለይም በኀይል አቅርቦት ላይ የተሠራው መዋቅራዊ ሥራ ነው” ያሉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል አሁን ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በተደረገ ንግግር የኀይል አቅርቦቱን ለመፍታት አስቸኳይ ሥራዎች ተሠርተዋል ብለዋል።
ለክልሉ የእድገት ማነቆ ኾኖ የያዘውን የመሰረተልማት ችግር ለመፍታትና ጸጋዎችን ተጠቅሞ እንዲለማ ርብርብ እየተደረገ ስለመኾኑም ነው የተናገሩት።
ባለሃብቶች በአካባቢው ያለውን የምርት አቅርቦት እሴት ጨምራችሁ ለገበያ እንድታቀርቡ፣ ለሀገር እድገትም አስተዋጽኦ እንድታደርጉ ጥሪ አቀርባለሁ ብለዋል።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ በክልሉ ያሉ ጸጋዎችን ለመጠቀምና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ላይ ታልሞ እየተሠራ እንደኾነ ነው የተናገሩት።
የክልሉ የኢንቨስትመንት ፍላጎት እያደገ ነው ያሉት ቢሮ ኀላፊው በቡሬ የተቀናጀ የግብርና መርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ አስፈላጊው መሰረተልማት እየተሟላለት ነው ብለዋል። ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኩ ገብተው አዲያለሙ ጥሪያችንን እናቀርባለን ብለዋል።
ክልሉ ለባለሃብቶች ምቹ ሁኔታዎችን በማመቻቸት፣ ማበረታቻዎችን መስጠት ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ስለመኾኑም ነው የተናገሩት።
የቡሬ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክን የማስተዋወቅና ባለሃብቶችን የመሳብ ታላቅ ፎረም በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል። በፎረሙ ክልሉ በአግሮ ኢንዱስትሪው ልማት ያለው አቅምና ባለሃብቶች መጥተው መዋዕለንዋያቸውን ቢያፈሱ ያለውን ምቹ ሁኔታ የሚገልጹ ጹሑፎችም ለውይይት ቀርበዋል።
በፎረሙ የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ ባለሃብቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተግኝተዋል።
ዘጋቢ:- ጋሻው አደመ
ፎቶ ፦ ብሩክ ተሾመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን‼