የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የሚገነባ የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ ሥራ አስጀምረዋል።

0
227

ባሕር ዳር፡ ሕዳር 20/2012ዓ.ም (አብመድ) ከተንታ መገንጠያ – ወገል ጤና – ኩርባ (ዳውንት) መገንጠያ የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ ሥራ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ ለወረዳዋ ዕድገት ከአስፓልት መንገዱ በተጨማሪ ወደ ቀበሌዎችና ሌሎች አጎራባች አካባቢዎች የሚያገናኙ የጠጠር መንገዶችን ማጠናከር እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

‹‹ልማት ላይ እንዳናተኩር ተብትበው የሚዙን ብዙ ቢሆኑም ሠላማችን በየአካባቢያችን መጠበቅ ከተቻለ ብዙ ጥያቄዎች ይፈታሉ›› ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ ‹‹የመንገድ ፕሮጀክቱ 79 ነጥብ 24 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ነው፤ 1 ቢሊዮን 873 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚገነባ ነው›› ብለዋል።
የሚገነባ የመንገድ ፕሮጀክት ሦስት ዓመታትን እንደሚወስድም የተናገሩት ዳይሬክተሩ የደሴ፣ ላልይበላ፣ ሰቆጣ ፣ ዓብይ አዲ መንገድ አካል የሆነ ስትራቴጂክ ፕሮጀክት መሆኑንም ገልጸዋል።

ወጪው በኢትዮጵያ መንግሥት የሚሸፈነው የተንታ መገንጠያ – ወገል ጤና – ኩርባ (ዳውንት) የመንገድ ፕሮጀክት ሰሜን ወሎን ከደቡብ ወሎ ማገናኛ አማራጭ መንገድ ነው።

ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ ለሚሄዱ ምዕመናን እና ቱሪስቶች ምቹ አማራጭ ፣ ለአካባቢው የግብርና ምርት በቀላሉ ወደ ገበያ ማዳረሻና ለመሠረተ ልማት ማሳለጫ ሌላ ምቹ ቀጠናን የሚፈጥርም ነው።

የኢፌዴሪ ትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ መንገዱ በተገቢው ጥራትና ፍጥነት እንዲጠናቀቅ የአካባቢው ማኅበረሰብ እና አማካሪ ድርጅቱ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡም ጠይቀዋል።

ዘጋቢ፦ ግርማ ተጫነ -ከዳውንት

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here