የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ያስተላለፉት መልእክት።

123
ነጭመደበኛ
ነጭመደበኛ

እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ!

የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትርጉሙ የላቀ ነው። ጨለማ፣ በደልና የሞት ጥላ ተሽረው ብሩህ ተስፋ፣ ነጻነት ፣ ፍቅርና ለሰው ልጆች ሁሉ ዘላለማዊ ሰላም የተገኘበት አዲስ ምዕራፍ ነው።

በልደቱ ያገኘነው ሰላም፣ ነጻነት፣ ብርሃንና ፍቅር ዋጋ የተከፈለበት፤ ሞትን በመወለዱ ያሸነፈበት መሆኑ ይታመናል። በመወለዱ ያገኘነው ነጻነትና ሰላም እንደመሆኑ እንደ ሀገር ከዚህም ከዚያም የሚስተዋሉ ችግሮችን ከቂምና በቀል ተላቀን በውይይትና በመነጋገር ቀርፈን የአገራችን ሰላምና አንድነት ማረጋገጥ ይኖርብናል።

የኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት የሚጸናው በሕዝቦቿ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ላይ ነው። ያለፈተና ድል፣ ያለጽናት አሸናፊነት አይታሰብም። ፈተናዎቻችን ሁሉ በአሸናፊነት የምንሻገረው ግን ተነጣጥለን ሳይሆን በመተሳሰብ በአንድነት መቆም ስንችል መሆኑን መረዳት ይገባል።

የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት የሚገነባው እንደሀገር በጋራ በምናደርገው ውይይት ላይ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው። በጋራ ካልተወያየንና ካልተግባባን ችግሮቻችንን በዘላቂነት መፍታት አንችልም። ጠላቶቻችን ብዙና ተለዋጭ ናቸው። የጠላቶቻችን ተለዋዋጭ ሴራ በማክሸፍ የሕዝባችንን ሰላም የምናረጋግጠው በመደማመጥ አንድ ስንሆን ነው።

ስለሆነም ከምንጊዜም በላይ አንድ ሁነን ሀገራችን በጋራ እናጽና እያልኩ ለመላው የእምነቱ ተከታዮች በዓሉ የሰላም፣ የደስታ፣ የፍቅር፣ የመተሳሰብና የአንድነት እንዲሆን በራሴና በክልሉ መንግሥት ስም እመኛለሁ።

መልካም በዓል!

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!