የአማራ ክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ በመስክ ምልከታው የተፈናቃዮችን ወቅታዊ ኹኔታም ይመለከታል ተብሏል።

0
54

ባሕር ዳር :ጥር 14/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች ቡድን የሚከታተሏቸውን ተቋማት የ2015 ዓ.ም የግማሽ ዓመት ሥራ አፈጻጸም የአካል ምልከታ እንደሚያደርግ አስታውቋል። ከጥር 14/2015 ዓ.ም እስከ ጥር 29/2015 ዓ.ም ለተከታታይ 16 ቀናት በሚያደርጉት የመስክ ምልከታ ስድስቱም የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች እስከ ቀበሌዎች ድረስ ወርደው አሰፈጻሚውን እና ተገልጋዩን እንደሚያነጋግሩ የቋሚ ኮሚቴዎች አስተባባሪ ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት ከተሰጡት ተግባር እና ኅላፊነቶች መካከል አንዱ የሚከታተላቸውን ተቋማት ቁጥጥር እና ክትትል ማድረግ ነው ያሉት የአማራ ክልል ምክር ቤት የሰው ሃብትና ቱሪዝም ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የቋሚ ኮሚቴዎች አሥተባባሪ ወይዘሮ አበራሽ ታደሰ ናቸው።

ምክር ቤቱ ቀደም ብሎ የኹሉንም ሴክተር መሥሪያ ቤቶች የ2015 ዓ.ም የሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ተቀብሎ እና ገምግሞ ግብረ መልሶችን ሰጥቷል ያሉት ወይዘሮ አበራሽ ፤ የስድስት ወር የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቶችን ተቀብሎ መገምገሙንም ገልጸዋል። የመስክ ምልከታው ዓላማም የቀረበለትን ሪፖርት ተግባራዊ አፈጻጸም እስከታች ወርዶ ማረጋገጥ ነው ብለዋል።

በስድስት ወር አፈጻጸም የታዩ ጥንካሬዎችን እና ድክመቶችን በመለየት በየደረጃው ውይይት ይደረጋል ያሉት አሥተባባሪዋ በየደረጃው ያልተፈቱ ችግሮችን ለቅሞ በመያዝ በቢሮ ደረጃ ከቢሮ ኅላፊዎች፣ ምክትል ኅላፊዎች እና የሥራ አመራር ቡድኖች ጋር እንደሚመክር ጠቁመዋል። በዚህ ኹሉ ሂደት ውስጥ የማይፈቱ ችግሮች ካሉም ቋሚ ኮሚቴው ለምክር ቤቱ የውሳኔ ሃሳብ ያቀርባል ተብሏል።

ምክር ቤቱ በመስክ የአካል ምልከታው 9 ዞኖችና ከተማ አሥተዳደሮችን፣ 18 ወረዳዎችን እና 36 ቀበሌዎችን ይመለከታል ያሉት ወይዘሮ አበራሽ የተመረጡት ቀበሌዎች እና ክፍለ ከተማዎች ከዚህ ቀደም በምልከታ ያልታዩ አካባቢዎች እንዲኾኑ ጥረት ተደርጓል ነው ያሉት።

በመስክ ምልከታው እንደ ሀገር የወጡ ሕጎች፣ መመሪያዎች፣ ደንቦች፣ ስትራቴጅዎች እና የአሠራር መመሪያዎች በታለመላቸው ልክ ያላቸውን ተግባራዊ አፈጻጸም ይመለከታል ያሉት አስተባባሪዋ በመንግሥት አስፈጻሚ ተቋማት መካከል ያለው ቅንጅታዊ አሠራርንም ይመረምራል ብለዋል።

በምክር ቤቱ የቋሚ ኮሚቴዎች ምልከታ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ዙሪያ በማረሚያ ቤቶች እና በፖሊስ ጣቢያዎች ከታራሚዎች እና በሕግ ጥላ ስር ካሉ ዜጎች ጋርም ይወያያል ያሉት ወይዘሮ አበራሽ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ወገኖችን ወቅታዊ ኹኔታም ይመለከታል ብለዋል።

ግብርና፣ ጤና፣ ትምሕርት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የመሠረተ ልማት ግንባታ፣ አገልግሎት አሰጣጥ፣ የኢንዱስትሪ መንደሮች፣ ሠላምና ደህንነት፣ ሴቶችና ሕጻናት፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ፣ የተፈናቃዮች ወቅታዊ ኹኔታ እና የወጣቶች መዝናኛ ማዕከላት ግንባታ የምልከታው ትኩረቶች ናቸው ተብሏል።

በየአካባቢው የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች፣ የመልካም አሥተዳደር ችግሮች እና የአገልግሎት አሰጣጥ ፈተናዎች ሕዝቡን ሲያማርሩት ይደመጣል ያሉት ወይዘሮ አበራሽ የቋሚ ኮሚቴዎቹ የመስክ ምልከታ ለምክር ቤቱ ውይይት እና የቀጣይ ጊዜያት አቅጣጫዎች የውሳኔ ሃሳብ ለማቅረብ ያግዛል ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!