የአማራ ክልልን ኢንቨስትመንት ለማሳደግ የክልሉ መንግሥት ከባለሀብቶች ጋር በቅርበት እንደሚሠራ ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ ገለፁ።

0
118

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 27/2014 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ በክልሉ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን በተመለከተ ከባለሀብቶች እና ሌሎች አጋርና ባለድርሻዎች ጋር በባሕር ዳር ውይይት እያካሄደ ነው።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) የክልሉ መንግሥት በተለያዩ ከተሞች ከ3 ሺህ 200 በላይ ሄክታር ላይ 28 የኢንዱስትሪ መንደሮችን በመገንባት ለባለሀብቱ ማስረከቡን ተናግረዋል፡፡ ክልሉ ለኢንዱስትሪ ፓርኮቹ የኀይል አቅርቦት እንዲሟላ በማድረግ፣ የብድር አገልግሎትን በማቅረብ የኢንቨስትመንት ዘርፉ እንዲለማ ማድረጉን ርእሰ መሥተዳድሩ ገልጸዋል፡፡ በክልሉ ለባለሀብቱ የሚደረገው ድጋፍ በትኩረት መሠራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በርካታ ባለሀብቶች የልማት ቦታ ቢሰጣቸውም የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት መወጣት አለመቻላቸውን ርእሰ መሥተዳድሩ ተናግረዋል። የኢንቨስትመንት ችግሮች በፍጥነት እንዲሻሻሉ ባለሀብቶችም ለሕዝብ ቃል የገቡትን የሥራ እድል መፍጠር ሥራ፣ በብቃት መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል። በየደረጃው የሚገኙ የፌዴራልና የክልሉ የሥራ ኀላፊዎች የዘርፉን ማነቆ ለመፍታ በጋራ መሥራት እንዳለባቸው አብራርተዋል፡፡ መንግሥት ከባለሀብቱ ጋር በቅርበት ይሠራል፣ ይደግፋልም ነው ያሉት። ርእሰ መሥተዳድሩ “በክልሉ በኢንቨስትመንት መስክ የተሰማሩ ባለሀብቶች የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት ሊወጡ ይገባል፤ ዘርፉን ለማሳደግም መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል” ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ ባለፉት ዓመታት የክልሉ መንግሥት ለኢንቨስትመንት ንቅናቄው ትኩረት ሰጥቶ ሲሠራ እንደቆየ ተናግረዋል። ባለሀብቱ የኦንላይን አገልግሎት እንዲያገኝ መደረጉንም ጠቅሰዋል። አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት እንደሚገባውም ኀላፊው ገልጸዋል።
በክልሉ የኀይል አቅርቦት መኖሩን ያነሱት አቶ እንድሪስ በርካታ ባለሀብቶች ማሽን በመትከል ወደ ሥራ እንዳይገቡ የኀይል አቅርቦት ችግር እንደገጠማቸው አስረድተዋል። 937 የሚኾኑ ባለሀብቶች የተሰጣቸውን መሬት አጥረው መቀመጣቸውንም ጠቁመዋል። በእነዚህ ባለሀብቶች ላይ እርምጃ ቢወሰድም የተለያየ ምክንያት እንደሚያቀርቡ አቶ እንድሪስ ተናግረዋል።
አንዳንድ ባለሀብቶች የተሰጣቸውን የብድር አገልግሎት ላልተፈለገ ዓላማ እንዳዋሉት ኀላፊው ገልጸዋል። በክልሉ የሚገኙ በርካታ ኢንዱስትሪዎች የግብዓትና የውጭ ምንዛሬ ችግር እንዳለባቸውም ነው የጠቆሙት፡፡
➡780 የተለዩ ፕሮጀክቶች መሬት ቢያገኙ፣
➡የተሰጣቸውን መሬት አጥረው የተቀመጡ 937 ባለሀብቶች ችግራቸው ተለይቶ ወደ ሥራ እንዲገቡ ቢደረግ፣
➡399 ፕሮጀክቶች የኀይል አቅርቦት ችግር ቢፈታላቸው፣
➡347 ፕሮጀክቶች የብድር አገልግሎት ቢያገኙ፣
ለ125 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ እድል ከመፍጠር ባለፈ የክልሉ ኢንዱስትሪ ሊበለጽግ እንደሚችል ኀላፊው አመላክተዋል። ስለኾነም ሁሉም ባለድርሻ አካላት የተጠቀሱትን ችግሮች በቅንጅት እንዲፈቱም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
#ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ
#ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
#የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
#ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/336LQaS
ቲክቶክ https://bit.ly/32rKF5J
በአሸባሪውና ወራሪው የትግራይ ቡድን በሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ ላልይበላ፣ ደሴ እና ከሚሴ አካባቢዎች የወደሙና የተዘረፉ የሚዲያ መሳሪያዎችን መልሶ በመገንባት ለሕዝብ አገልግሎት ለመስጠት አሚኮን ይደግፉ።
https://ameco.bankofabyssinia.com/